ሰኔ 2 2017 በአጎዋ ዕድል መታገድ እና በቅርቡም የአሜሪካ መንግስት በጣለው የ10 በመቶ ታሪፍ ምክንያት 16 በመቶ ታክስ እየተከፈለበት ወደ አሜሪካ የሚላከው የኢትዮጵያ አበባ ተጽዕኖ አርፎበታል ተባለ፡፡
- sheger1021fm
- Jun 9
- 1 min read

በመሆኑም ኢትዮጵያ ለአበባ ምርቷ በአፍሪካ ፤ በመካከለኛው ምስራቅ እና በአውሮፓ ሀገራት አማራጭ ገበያ እያፈላለገች መሆኗ ተሰምቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ አሜሪካ ምርቶቻቸውን በሚልኩ 100 ሀገራት ላይ ታሪፍ መጣላቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ላይ የተጣለው ታሪፍ 10 በመቶ ነው ።
ቀደም ሲልም የአፍሪካ ሀገራት የተለያዩ ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ እንዲያስገቡ ከተሰጠው ዕድል ወይም አጎዋ ኢትዮጵያ መታገዷ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከአጎዋ ዕድል የተሰረዘችው ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተገናኘ፣ በመንግሥትና በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ አካላት ሰበብ በተፈጠሩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በእነዚህ ሁለት የአሜሪካ መንግስት ውሳኔዎች ምክንያት ተፅዕኖ ካገኛቸው መካከል ደግሞ የአበባ፤ ዘርፍ አንዱ መሆኑ ተነግሯል።
ኢትዮጵያ ከአጎዋ ዕድል ከታገደች በኋላ ስድስት በመቶ ታክስ እየከፈለች ምርቱን ስትልክ እንደቆየች የሚያስታውሱት፤
የኢትዮጵያ አበባ ፤ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች እና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ፤
የፕሬዝዳንት ትራምፕን ውሳኔ ተከትሎ ደግሞ የምንከፍለው ታክስ ወደ አስራ ስድስት በመቶ ከፍ አድጓል ሲሉ ተናግረዋል።
ተፅዕኖውን ለመቋቋም ለኢትዮጵያ የአበባ ፤ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ተጨማሪ ገበያዎችን እያፈላለግን ነው ሲሉም አቶ ቴዎድሮስ ነግረውናል
ምርቶቹን ወደ አፍሪካ ፤ መካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓ ሀገራት በስፋት ለመላክ ስራ ጀምረናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከላከችው አበባ እስከ 45 ሚሊየን ዶላር ስታገኝ መቆየቷ ተነግሯል።
ኢኳዶር እና ኮሎምቢያ በአሜሪካ ገበያ ኢትዮጵያን በአበባ ምርት የሚፎካከሩ ሀገራት እንደሆኑ ተጠቅሷል።
ኢኳዶር ልክ እንደ ኢትዮጵያ የ10 በመቶ ታሪፍ በፕሬዝዳንት ትራምፕ የተጣለባት ሲሆን የኮሎምቢያ ደግሞ 16 ነጥብ 8 በመቶ ነው።
ሁለቱ ሀገራት ለአሜሪካ ለአሜሪካ ቅርብ በመሆናቸው የትራንስፖርት ወጪያቸው አነስተኛ እንደሆነ ነው የተነገረው።
ይህም የተጣለውን ታሪፍ ተቋቁመው በአሜሪካ ገበያ እንዲቆዩ ሊረዳቸው ይችላል ተብሏል።
ንጋቱ ረጋሣ
Comments