top of page

ሰኔ 19 2017 - የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ የተሰጠው የ6 ወር የሽግግር ጊዜ፤ ከ5 እስከ 7 ዓመት እንዲራዘም ተጠየቀ

  • sheger1021fm
  • Jun 26
  • 2 min read

በቅርቡ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የፀደቀው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ የተሰጠው የ6 ወር የሽግግር ጊዜ፤ ከ5 እስከ 7 ዓመት እንዲራዘም ተጠየቀ።


ይህን የጠየቀው የኢትዮጵያ ፕላስቲክና ጎማ አምራቾች ዘርፍ ማህበር ነው።


የፕላስቲክ ምርት ዘርፉ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ፈሰስ በማድረግ ጉልህ ሚና አለው ያለው ማህበሩ፤ ሆኖም በ6 ወር ውስጥ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግሉ ፌስታሎችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች እንዲቆም አዋጁ መፅደቁ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ቀውስ ስለሚያስከትል መንግስት ማጤን እንደሚገባውም ማህበሩ ጠይቋል።


መንግስት የፕላስቲክ ብክለትን በተመለከተ ስጋት ካለው ከጤና ሚኒስቴር፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና ከሌሎች ተጠሪ መስሪያ ቤቶች የተውጣጣ ተቆጣጣሪ አካል በማቋቋም ራሱን የቻለ ቁጥጥር እያደረገ ዘርፉ ማምረቱን ቢቀጥል ሲል ማህበሩ እንደ መፍትሄ ሀሳብ አቅርቧል።


ሆኖም ምርቱ መቀጠል የለበትም ከተባለም የተሰጠው የ6 ወር የሽግግር ጊዜ እጅግ ያነሰና ምንም ለማሰብ ፋታ የሚሰጥ ባለመሆኑ ባለሀብቱ ከባንክ የተበደረውን ብር ሰርቶ እስኪከፍል እና ሌሎች ነገሮችን እስኪያመቻቹ ድረስ ከ5 እስከ 7 አመት የሽግግር ጊዜ እንዲፈቀድ ማህበሩ ጠይቋል።


አዋጁ አምራቾችን ስጋት ላይ የጣለ ነው ያለው ማህበሩ በፕላስቲክ አመራረትና አጠቃቀም ላይ አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ውለው የሚጣሉ በሚል የተገለፀው እንዲሁም ለአዋጁ መፅደቅ ምክንያት የሆነው ሀሳብ ከግንዛቤ እጥረት አንዳይሆን ሲል ማህበሩ ተናግሯል።


ማህበሩ አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ውሎ የሚጣል የፕላስቲክ ከረጢት የለምም ብሏል።


መንግስት ከህብረተሰቡ የእለት ከእለት ኑሮ ጋር የተቆራኘውን የፕላስቲክ ከረጢት የሚተካ በቂና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ግብአት አዘጋጅቷል ወይ ሲልም ማህበሩ ጠይቋል።


ማህበሩ አክሎም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚሊዮን የሚቆጠር የስራ እድል የፈጠረው ዘርፍ ሲዘጋ ከዚህ ስራ የሚፈናቀሉ ሰዎች ዕጣ ፋንታ ምን ሊሆን ይችላል ሲልም አስረድቷል፡፡


በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ከ500 በላይ ፋብሪካዎች ለማስፋፊያና ስራውን ለማዘመን ከባንክ ተበድረው ያስገቧቸው አዳዲስ ማሽነሪዎች እና የማስፋፊያ ግንባታዎች ጉዳይ ዕጣፋንታው ምን ይሆናል? ምርት ካቆሙስ ምን ሰርተው የባንክ እዳ ይከፍላሉ የሚለውን መንግስት ሊያጤነው ይገባል ሲል ማህበሩ ጠይቋል።


በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች በበኩላቸው አዋጁ የከለከለውን ምርት እንዳናመርት ከታገድን መንግስት ሌላ አመራጭ የስራ ዘርፍ ሊፈጥርልን ይገባል ብለዋል።


( ተያያዥ ዘገባን ለማንበብ… https://tinyurl.com/2a9k57yd )


ፍቅሩ አምባቸው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page