top of page

ሰኔ 19፣ 2016 - የውጭ ሀገር ባንኮች ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ በሃገር ውስጥ ያሉ ባንኮች ከውድድር ሜዳው ይወጣሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው የም/ቤት አባላት ተናገሩ

የውጭ ሀገር ባንኮች ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ በሃገር ውስጥ ያሉ ባንኮች ከውድድር ሜዳው ይወጣሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው የምክር ቤት አባላት ተናገሩ፡፡


የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው ስብሰባ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበለትን የውጭ ባንኮች በሀገሪቱ እንዲሠማሩ የሚፈቅደው የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል፡፡


በዚህም ወቅት የውጭ ሃገር ባንኮች የሃገር ውስጥ የባንክ ገበያን እንዲቀላቀሉ ሲፈቀድ የዘመነ የባንክ አሰራርና የውጭ ምንዛሪን ያመጣሉ በሚል ታምኖባቸው ቢሆንም የሀገር ውስጥ ባንኮች የመወዳደር አቅም ላይ ጥያቄ አለን፣ እንዳያከስሟቸውም እንሰጋለን ብለዋል የምክር ቤት አባላቱ፡፡


የምክር ቤት አባላቱ በተጨማሪም የገበያ ውድድሩን ሚዛን ለመጠበቅ ወደ ስራ የሚገቡትን የውጭ ሃገራት ባንኮችን ለመቆጣጠር አሰራር መዘርጋት አለበት፤ የሀገር ውስጥ ባንኮችም አቅማቸውን እንዲያሻሽሉ መታገዝ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡


በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ በቀረበው የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡


የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት ሲያስረዱ ላለፉት 16 ዓመታት ሲሰራበት የነበረውን የባንክ አዋጅ ማሻሻል ያስፈለገው የውጭ ሃገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዘርፉ እንዲሰማሩ፤ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ዝግ ተደርጎ የቆየውን የውጭ ሃገራት ባንኮች ወደ ሃገር ቤት ገብተው እንዲሰሩ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑን ተከትሎ አዋጁን ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል፡፡


ለምክር ቤቱ የቀረበው የተሸሻለው የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለዝርዝሩ እይታ ለፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡


ምንታምር ፀጋው



Commentaires


bottom of page