ሰኔ 19፣ 2016 - የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት ዘርፍ አሁንም ፈተናዎች አላጡትም
- sheger1021fm
- Jun 26, 2024
- 1 min read
ከዓመት ዓመት የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉለት ነው የሚባለው የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት ዘርፍ አሁንም ፈተናዎች አላጡትም፡፡
በየጤና ተቋማቱ የሚፈለጉ መድኃኒቶች እንደልብ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ዘልቋል፡፡
ከዓለም አቀፍና ከሀገር ቤት አቅራቢዎች በጨረታ መድኃኒት የምትሸምተው ኢትዮጵያ በተጨማሪም የሀገር ቤት አምራቾችን በማበርታት በዘርፉ የሚታየውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት እንድትሰራ ተመክራለች፡፡
ለብዙ ዓመታት በመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓቱ ውስጥ ከሚነሱ ችግሮች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዋነኛው ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ይህም ከውጭ የሚገዙትን ጨምሮ ለሀገር ቤት የመድኃኒት ምርቱም ዋነኛ ፈተና መሆኑ ተነግሯል፡፡
በጤና ሚኒስቴር በተዘጋጀው የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት ምርትና ኢኖቬሽን ኤግዚቢሽን ላይ በተሰናዳ አውደ ጥናት ላይ ነው ይህ የተነገረው፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በተሰራ ምዘና የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርቱ 24 በመቶ እንደነበር የሚጠቅሱት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሴ ነገር ግን በየዓመቱ ድርሻው በመቀነስ ባለፈው በጀት ዓመት 6 በመቶ ደርሶ ነበር ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በግዢ ሥርዓት ውስጥ ከሚፈለጉ መድኃኒቶች በቂ አቅራቢ ያላቸው 20ዎቹ ብቻ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ከውጭ አቅራቢዎችም ይሁን ከሀገር ቤት አምራቾች በቂ ምርት ለማግኘት በተለይ የሀገር ቤት አቅራቢዎች ለማበረታታት ቀደም ሲል የተነሱትን ችግሮች ለማስተካከል የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንዲስተካከል እያደረግን ነው ብለዋል አቶ ሰለሞን፡፡
በሀገር ቤት መዋለ ነዋያቸውን አፍስሰው የመድኃኒት ምርት ኢንዱስትሪውን የተቀላቀሉ አምራቾች በበኩላቸው ዘርፉ በርካታ ችግሮች ያሉበት የምርት ድርሻውም ከሚጠበቀው እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ እንደነበረም ተጠቅሷል፡፡
አሁን በተደረጉ ድጋፎች የተገኙ ለውጦች አሉ የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የመድኃኒት አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንቱ አቶ ሰለሞን ገ/አማኑኤል ናቸው፡፡
ምርቱ በሀገር ውስጥ ይሆናል ቢባልም እያንዳንዱ ግብዓት ማሸጊያ ካርቶን እንኳል ሳይቀር በውጭ ምንዛሬ የሚገኝ መሆኑ ዋናው ችግር መሆኑም ተነግሯል፡፡
የተወሰኑት እዚሁ ማግኘት የሚቻሉ ግብዓቶች ማቅረብ ቢቻል ችግሩን ማስተካከል ይቻላልም ተብሏል፡፡
ምህረት ስዩም
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Comments