ሰኔ 18 2017 - የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መንግስትን ከ9 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ወጭ እንዲያወጣ አድርጓል ተባለ
- sheger1021fm
- Jun 25
- 2 min read
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የእርዳታ ማከማቻ መጋዘኖች ግንባታ በታቀደው ጊዜ ባለማለቁ መንግስትን ከ9 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ወጭ እንዲያወጣ አድርጓል ተባለ፡፡
በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ላሉ ከሶስት ሚሊየን በላይ ተፈናቃዮችም የተመደበው የሰብአዊ እርዳታ እየቀረበላቸው አለመሆኑን የ2016 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት አሳይቷል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በበጀት ዓመቱ ያካሄደውን የፋይናንስ ህጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ግንቶቹን በሪፖርት መልክ አሰናድቶ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡
በዚሁ ዳጎስ ባለው የኦዲት ሪፖርት በተለያዩ 39 መ/ቤት ላይ የክዋኔ ኦዲት ማካሄዱን ጠቅሷል፡፡
ከመካከላቸው #የኢትዮጵያ_አደጋ_ስጋት_አመራር_ኮሚሽን 2738 መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ላሉ ከ3 ሚሊየን 306 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች የተመደበውን የሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ እያቀረበላቸው አይደለም ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል እርዳታ ከሚቀርብላቸው ተፈናቃዮች መካከል 15 በመቶው ወይንም 489290 ያህሉ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ናቸው፤ የተባለ ሲሆን ማግኘት ያለባቸውን አልሚ ምግቦች ኮሚሽኑ ለሁሉም ተረጂዎች ስለሚያከፋፍለው ህፃናት፣ የሚያጠቡ እና ነፍሰ ጡር እናቶች የሚገባቸውን አልሚ ምግብ ሳያገኙ ቀርተዋል ይላል የኦዲት ሪፖርቱ፡፡
እንደ በቆሎ፣ አኩሪ አተር ያሉ ቅይጥ ምግቦች ናቸው ያለምንም ተጨማሪ መስፈርት ለሁሉም ተረጂዎች የተከፋፈሉት ፤ የሚገባቸው ሕፃናትና እናቶች አልሚ ምግብ እንዲያገኙ ይገባ ነበር የተባለው፡፡
አልሚ ምግቡም በአፋጣኝ እየተተካ አለመሆኑም ሌላኛው ችግር ሆኖ ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም በናሙና ተመርጠው ምርመራ በተደረገባቸው በሐረሪ (ሐማሬሳ) የመጠለያ ጣቢያ እና በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞን በታዩ ሁለት ወረዳዎች ባሉ 10 መጠለያ ጣቢያዎች አልሚ ምግብ ከተቋረጠ ከ2 ዓመት በላይ ሆኖታል ተብሏል፡፡
በመጠለያ ጣቢያዎቹም ውሃ፣ መብራትና የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት ለረዥም ጊዜ የተቋረጠ መሆኑን ዋና ኦዲተር መ/ቤት አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
እንዲሁም የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በቂ አይደለም የተባለው የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶችን እርዳታ ለክልሎች ከላከ በኋላም በትክክል ለተፈናቃዮቹ ስለመድረስ እና ስለመከፋፈሉ ክትትል አያደርግም ተብሏል፡፡
ለዚህም የዘረጋው አሰራር የለም ይላል የኦዲት ሪፖርቱ፡፡
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ በቀብሪ ዳሃር፣ ፍኖተ ሰላምና ሆሳዕና ከተሞች የእርዳታ ማከማቻ የመጋዘን ግንባታ መጀመሩ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
ይሁንና የመጋዘኖቹ ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት ባለመጠናቀቁ መንግስት ተጨማሪ ከ9 ቢሊየን ብር በላይ እንዲያወጣ ምክንያት መሆኑም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ከተደረገባቸው ተቋማት ሌላኛው የ #ውሃና_ኢነርጂ_ሚኒስቴር መ/ቤት ነው፡፡

ሚኒስቴሩ የሚያስገነባቸው ሶስት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ላይም ፍተሻ ተደርጓል፡፡
ጊዶሌ፣ ወንጂ እና ዶንጎራ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ የአዋጭነት ጥናቱን በተመለከተ የተከወኑ ስራዎችን እና የፕሮጀክቱን የገንዘብ አያያዝም በተመለከተ ኦዲት ተደርጓል፡፡
በዚህም ለጊዶሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተገዝተው የመጡ የቧንቧ አቅርቦትና መገጣጠሚያ እቃዎች ወደብ ላይ ከደረሱ በኋላ በ15 ቀን ጊዜ ወደ ሀገር መግባት ሲጠበቅባቸው 257 ቀናት ወደብ ላይ በመቆየታቸው ኢትዮጵያ ተጨማሪ 11.4 ሚሊየን ብር ለኮንቴነር እና ለመጋዘን ኪራይ መክፈሏ ተረጋግጧል፡፡
በተጨማሪም የውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታ 72 በመቶ ከደረሰ በኋላ የዲዛይን ማሻሻያ በመደረጉ ፕሮጀክቱ ከተያዘለት በጀት ከ25.6 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሁም ሌላ በዶላር ከ250,000 ዶላር በላይ ተጨማሪ ወጭ መጠየቁም በሪፖርቱ ሰፍሯል፡፡
በሌላ በኩል የሚኒስቴር መ/ቤቱ ለሚያስገነባቸው የመንጆና ዶንጎራ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በቂ የቅደፍመ አዋጭነት ጥናት ባለመካሄዱ የመንጆ የውሃ መገኛ ጉድጓድ መክኗል ተብሏል፡፡
የጎንዶራ ውሃም ለመጠጥ አገልግሎት መዋል የማይችል መሆኑ ተረጋግጦ ታሽጓል መታሸጉን ከኦዲት ሪፖርቱ ተመልክተናል፡፡
ለዚህም የወጣው ወጭ ከ16 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑን ሰምተናል፡፡
መክኗል የተባለው የመንጆ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ56 ሚሊየን ብር በላይ የወጣበት ነበር ተብሏል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
コメント