ሰኔ 18 2017 - ኢትዮጵያ በህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ በወር 19 ሚሊየን ዶላር ያህል እንደምታጣ ጥናቱ አሳይቷል
- sheger1021fm
- Jun 25
- 2 min read
የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ በርካታ ችግሮች ያሉበት እንደሆነ ተደጋግሞ ይነሳል።
ኮንትሮባንድ፣ የግብይት ስርአቱ ደካማ መሆን፣ የእንስሳት ማቆያ ቦታዎች በበቂ መጠን አለመኖር እንዲሁም የህክምና እና የዕርድ ማዕከላት በሚገባው ደረጃ አለመገኘት የዘርፉ ችግሮች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።
በዚህም ምክንያት እስከ 150 ሚሊየን ዶላር ሲገኝበት ነበር የሚባለው የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ንግድ እያሽቆለቆለ መጥቶ 2014 እና 2015 ላይ 17 ሚሊየን ዶላር ወርዷል።
በሶስት የመውጫ በሮች በተደረገ ጥናት በቀን ከ1200 በላይ #የቁም_እንስሳት በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንደሚወጡ በአንድ ወቅት ይፋ በሆነ ጥናት ተመልክቷል።
በዚህም ኢትዮጵያ በቀን ከ630 ሺህ ዶላር በላይ ፤ በወር ደግሞ 19 ሚሊየን ዶላር ያህል በህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ምክንያት እንደምታጣ ጥናቱ አሳይቷል።
ዘንድሮ ግን ይህ ህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ የተወሰነ መቀነስ ማሳየቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሰሞኑ ያወጣው መረጃ ይጠቁማል።
በ2017 በጀት ዓመት 11 ወራት 59 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወደ ውጪ ከተላኩ የቁም እንስሳት መገኘቱን የጠቀሰው የሚኒስቴሩ መረጃ ፤ገቢው በቀዳሚው 2016 ሙሉ የበጀት አመት ከተገኘው በሶስት እጥፍ የበለጠ ነው ብሏል።
በ2016 በጀት ዓመት ከቁም እንስሳት ወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 18 ሚሊየን ዶላር እንደነበር ከመረጃው ማወቅ ይቻላል።

ዘንድሮ ለታየው የቁም እንስሳት ህገ ወጥ ንግድ መቀነስ ዋና ምክንያት ተብሎ በሚኒስቴሩ የተጠቀሰው በውጪ ምንዛሪ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ነው።
የዘርፉ ችግር ግን የውጪ ምንዛሪ ብቻ እንዳልሆነ ይታወቃልና ሌሎቹስ ላይ ምን ተሰርቷል? ስንል ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ጥያቄ አንስተናል።
ወደ ውጪ የሚላኩ የቁም እንስሳት መጀመሪያ ወደ ማዕከል እንዲመጡ ይደረግ እንደነበር ያስታወሱት ስራ አስፈጻሚው ፤ለወደብ ቅርበት ባላቸው አካባቢዎች ማቆያዎችን በመስራት ያጋጥም የነበረውንም ችግር ለመቀነስ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ማዕከላት ከአርሶ አደሮች ፤ አርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች የቁም እንስሳቱ በግዥ የሚሰበሰቡባቸው እንደሆኑ ሠምተናል።
ሁለተኛ ደረጃ የግብይት ማዕከላት ደግሞ የቁም እንስሳቱ በቀጥታ ወደ ውጪ የሚላኩባቸው ዘመናዊ ማቆያዎች እንደሆኑ አቶ ወንድሙ ነግረውናል።
የቁም እንስሳቱን ከወደብ ራቅ ካሉ ቦታዎች ለማጓጓዝ የትራንስፖርት ክፍያው መወደድ ሌላው ችግር ሆኖ እንደቆየ የነገሩን አቶ ወንድሙ አሁን ለዚህም መላ ተበጅቷል ብለዋል።
አዳዲስ ሀገራት ከኢትዮጵያ የቁም እንስሳት መግዛት መጀመራቸውም የዘንድሮው ገቢ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተጠቅሷል።
ወደ ውጪ ከሚላኩ የቁም እንስሳት የሚገኘው ገቢ የተወሰነ መሻሻል አሳይቷል ቢባልም አሁንም ብዙ የሚቀረው እንደሆነ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ተናግረዋል።
እንሳስትን በቁም ወደ ውጪ መላክ በራሱ ብዙ አትራፊ አይደለም የሚሉት አቶ ወንድሙ የሚሻለው ስጋቸውን አዘጋጅቶና እሴት ጨምሮ መሸጥ ነው ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ዘመናዊ ቄራዎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተገነቡ እንደሚገኙ ነግረውናል።
በኮንትሮባንድ ወደ ተለያዩ ሀገራት የቁም እንስሳትን የሚልኩ ሰዎችን ለመቆጣጠር የሚከናወነው ስራም መጠናከሩ ስራ አስፈጻሚው ነግረውናል።
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments