ሰኔ 18 2017 - የፌዴራል ዋና ኦዲተር የተቋማትን ሪፖርት ሲያቀርብ የኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች ኃላፊዎች አለመገኘታቸው ጥያቄ ተነሳበት
- sheger1021fm
- Jun 25
- 2 min read
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የተቋማትን ሪፖርት ሲያቀርብ የኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች የመገኝት ሃላፊነት እያለባቸው አለመገኘታቸው በፓርላማ አባላት ዘንድ ጥያቄ ተነሳበት፡፡
እንዲህ ያለው ነገር ተጠያቂነትን ለማስፈን እንቅፋት ይሆናል ተብሏል፡፡
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ በበኩላቸው ሁሉም ኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤቶች እንዲገኙ ጥሪ መተላለፉን ተናግረዋል፡፡
ግን እንድም ሚኒስትር በኦዲት ሪፖርት ላይ አልተገኙም፡፡
ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት መ/ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት የፋይናንስ፣ የሕጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት አቅርቧል፡፡
ሪፖርቱን በንባብ ያቀረቡት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 190/2002 እና በፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሒሳብ አያያዝ መመሪያ ቁጥር 5/2003 መሰረት 137 መስሪያ ቤቶች እና 20 የገቢዎች እና የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በመመሪያው መሰረት እየሰሩ መሆኑን ለማረጋገጥ በተሰራው ኦዲት ወደ 33 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ያልተሰበሰበ ሂሳብ መኖሩ ተገረጋግጠዋል ብለዋል፡፡

የተሰብሳቢ ሂሳቡ በእድሜ በቆይታ ጊዜው ሲተነተን፤ ከአንድ ወር በላይ እስከ አንድ ዓመት 17.7 ቢሊዮን ብር ፣ከአንድ ዓመት በላይ እስከ አምስት ዓመት 10.4 ቢሊዮን ከአምስት ዓመት በላይ እስከ አሥር ዓመት ደግሞ 4.4 ቢሊዮን ብር መሆናቸው ታውቋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ከተገኘባቸው ተቋማት መካከል ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የጤና ሚኒስቴር 6.7 ቢሊዮን ብር ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር 1.7 ቢሊዮን ፣ የዋቻሞ ዩንቨርሲቲ 1.2 ቢልዮን ብር፣የትምህርት ሚኒስቴር 1.1 ቢሊዮን ከፍተኛውን ድርሻ የያዙ ተቋማት ናቸው፡፡
ዋና ኦዲተሯ ፤የግዢ አዋጅ ፣ደንብ እና መመሪያን ያልተከተለ ግዢ መፈጸሙን ለማረጋገጥ በተሰራ ኦዲት በ70 መስሪያ ቤቶች እና 7 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች 404.7 ሚሊዮን ብር ከመምሪያ ውጭ መፈፀሙን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
በወቅቱ ያልተከፈለ ውዝፍ ተከፋይ ሒሳብ በተመለከት በተደረገ ኦዲትም በ90 መስሪያ ቤቶች እና በ8 የጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤቶች በወቅቱ ያልተከፈለ 11.3 ብር ቢሊዮን ተከፋይ ሂሳብ መኖሩ ተጋግጧል፡፡
ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ፌዴራል መስሪያ ቤቶች የበጀት አጠቃቀማቸውን በተመለከተ በተደረገ ኦዲት 32 ተቋማት 1.6 ቢሊዮን ብር ከተደለደለላቸው በጀት በላይ መጠቀማቸውን የተናገሩ ሲሆን በበጀት ዓመቱ 14.4 ቢሊዮን ብር ድገሞ ስራ ላይ አለመዋሉ ተረጋግጠዋል ብለዋል፡፡
የኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርት ማብቀትን ተከትሎ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የምክር ቤት አባላት ጥያቄ እንዲቀርቡ እድል በሰጡበት ወቅት አንድ የምክር ቤት አባል የስነስረዓት ጥያቄ እንዳላቸው ተናግረው እድሉ በአፈ ጉባዔው «ሲሰጣቸው ሪፖርቱ ቀርቦልናል ኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤት የበላይ ሃላፊዎች በዚህ ስበሰባ ላይ በዚህ መድረክ ላይ መገኘት አልነበረባቸውም ወይ? አሁን ለማን ነው ጥያቄ የሚቀርበው የሚል ነገር ስላለኝ ነው »ብለዋል፡፡
«ብዙ ጊዜ የኦዲት ሪፖርት በሚቀርብበት ሰዓት ኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤቶች መገኘት እንዳለባቸው ሃሳብ ይሰጣል ነገር ግን ዛሬም እንደምናየው ኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤቶች የቀረቡበት ሁኔታ የለም እና በዚህ ጉዳይ ላይ ማሳሰብያ ቢሰጥ» ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ሌሎች የምክር ቤት አባላትም መሰል ጥያቄ አንስተዋል፡፡
ዋና አፈ ጉባዔው በበኩላቸው ሁሉም ኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤት መገኘት ነበረበት ጥሪም ተላልፏል ብለዋል፡፡
ስለዚህም ምክር ቤቱ እዚህ ሪፖርት ላይ መ ሰረተር በማድረግ በ2018 እቅድ ላይ አስገብቶ መስራትና ተጠያቂነትን ማስፈን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments