ሰዓዳ ሰይድ ሀገር ቤት ስራ መስራት ህይወቴን አይለውጠውም ብላ ወደ አረብ ሀገር ከተሰደደች አስር ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡
ሰአዳ የመጀመሪያ ጉዞዋ ህጋዊ ቢሆንም ተቀጥራ ስትሰራ የነበረችበት ቤት ስላልተመቻት ስትሰራ ከነበረበት በመጥፋት ሌላ ከተማ ውስጥ ገብታ እንደነበር ትናገራለች፡፡
በዚያ አይነት ሁኔታ ስራዋን እየከወነች ሶስት አመትን አስቆጥራ ነበር፡፡
ከዚያ በላይ ግን አልቆየችም 2013 ዓ.ም ወደ ሀገሯ እንደገባች ትናገራለች፡፡
ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰሰችው ሰአዳ ሰይድ ሀገሯ ላይ ከአንድ ወር በላይ የመቆየት እድል አላጋጠማትም፡፡
ሁኔታውን ሁሉ እንደጠበቀችው ባለማግኘቷ እና ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ ቢገባት ህገ-ወጥ ነሽ ተብላ ከተባረረችበት ሀገር ለመመለስ ወጥታለች፡፡
አካሄዷ ደግሞ በባህር ነው፤ በህገወጥ፡፡

የበረሃውን እና የባህር ስቃዩን አልፋ ካሰበችበት ሀገር ደርሳ ዓመት ከሶስት ወር ከሰራች በኋላ እንደገና ወደ እስር ቤት መግባቷን የምትናገረው ሰአዳ፤ በታሰረች በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባች ትናገራለች፡፡
የሁለት ዓመት ህፃን ልጇን ትታ በህገወጥ መንገድ ወደ ሳውዲ አረቢያ የሄደችው ሌላኛዋ የ19 ዓመቷ ሜሮን ሰማቸው ናት፡፡
ሜሮን ያሰበችው ሳይሆንላት ቀርቶ በሄደች በ10 ወሯ የጤና ችግር አጋጥሟት ከሁለት ወራት የእስር ቆይታ በኋላ ተመልሻለሁ ትላለች፡፡
ሰአዳ ሰይድ እና ሜሮን ሰማቸው ሀገራቸው ገብተው ታሪካቸውን ለመናገር በቁ እንጅ ቀን ፀሀዩ ማታ ውርጩ፣ ረሀቡ፣ የውሀ ጥሙ፣ ድካሙ በርትቶባቸው በየበረሃው ወደቀው የአሞራ ሲሳይ የሆኑ በባህር ሰጥመው የአሳ ነባሪ ቀለብ የሆኑት ደግሞ አይቆጠሩ፡፡
ከዛም አልፎ በየድንበሩ ለመሻገር ብር አምጡ እየተባሉ በህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ ጥቃት የሚደርስባቸው መኖራቸው በተደጋጋሚ የሚነገር ነው፡፡
መንግስትም በተለያዩ ጊዜያት በህገወጥ መንገድ ወደ አረብ ሀገራት የሄዱትን እና በየ እስር ቤቱ የሰነበቱ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ መከወን ከጀመረ ቆየት ብሏል፡፡

በዚህም በ2016 ዓ.ም ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ያደረኳቸው ኢትዮጵያውያን ከ95ሺህ በላይ ናቸው ብሏል፡፡
ኢትዮጵያውያኑንም ወደ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ከማድረግ ባለፈም በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል የስራ እድል እንዲፈጠር፤ የጤና እክል የሚገጥማቸውን ደግሞ ወደ ጤና ተቷማት በማስገባት እንዲያገግሙ እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ ይናገራል፡፡
በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴርም ከስደት ተመላሾች ስራ እንዲሰሩ የሚያደርጋቸውን የተለያዩ ድጋፎችን እየሰጠ እንዳለ ሰምተናል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የስራ እድል ተፈጥሮላቸው እየሰሩ ያሉ ከስደት ተመላሾችንም ሸገር ተመልክቷል፡፡
ተመላሾቹ እየሰሩት ያለው የንግድ ስራ ውጤታማ እያደረጋቸው እንዳልሆነ እና ወደ መጡበት ቦታ የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
ወደ ሀገር ቤት ሲመጡ ይሆናል ያሉት እና የሚያጋጥማቸው የተለያየ መሆንን ጨምሮ ሌሎችም ችግሮች ወደ ቤታቸው ተመልሰው የመጡት ኢትዮጵያውያን ተመልሰው በህገወጥ መንገድ እንደሚሄዱ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያኑንም ወደ ሀገር ቤት የመመለሱን ስራ የሚሰራው የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሀገራቸው ከገቡ በኋላ ተመለስው ወደ መጡበት በህገወጥ መንገድ መሄዳቸው አዳስ መንገደኞች ቁጥርም መቀንስ አለማሳየቱ ስራዬን ውሀ ቅዳ ውሀ መለስ ያደርግብኛል ብሏል፡፡

ተመላሾቹ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ስራ የመስራት ፍላጎት ማጣት፣ ወደመጡበት ሀገር ለመመለስ መፈለግ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት በመመለሱ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮች ናቸው ይላል የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡
በሚኒስቴሩ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል እና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍ እና ክትትል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጄ ተግይበሉ በህገወጥ መንገድ ከመጡት መካከል ተመልሰው የሚሄዱት ለማስቀረት እና አዲስ መንገደኞችን ለመቀነስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስራዎችን እየከወነ ነው ብለዋል፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Comments