top of page

ሰኔ 16 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Jun 23
  • 1 min read

አለም አቀፉ የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ(IAEA) በኢራን የኒኩሊየር ተቋማት ላይ በተፈፀመ ድብደባ የአደገኛ ጨረር ማፈትለክ አሳሳቢ አይደለም አለ፡፡


ከእስራኤል በተጨማሪ አሜሪካም የኢራንን የኒኩሊየር ተቋማት እየመታች መሆኑን አናዶሉ ፅፏል፡፡


IAEA የራዲዮ አክቲቭ አደገኛ ጨረሩን ሁኔታ እየተከታተልኩ ነው ማለቱ ተጠቅሷል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገራቸው ጦር የኢራንን የኒኩሊየር ተቋማት በተሳካ ሁኔታ መምታቱን ተናግረዋል፡፡


ኢራኖች ግን በኒኩሊየር ተቋሞቻችን ላይ ድብደባ ቢፈፅምም እምብዛም ጉዳት አልገጠማቸውም ብለዋል፡፡


አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን የኒኩሊየር ቦምብ ለመስራት እየተሯሯጠች ነው በሚል ሲከሷት ቆይተዋል፡፡


ኢራን በፊናዋ መርሐ ግብሬ ለኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ እና ለሰላማዊ አገልግሎት የታለመ ነው ስትል ትሟገታለች፡፡



ፓኪስታን አሜሪካ በኢራን ላይ የፈፀመችውን ድብደባ አምርራ አወገዘችው፡፡


የፓኪስታን ውግዘት የተሰማው የአገሪቱ መንግስት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት እጩ ይሁኑልኝ ባለ ማግስት እንደሆነ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


ትራምፕ ቀደም ሲል በሕንድ እና በፓኪስታን መካከል የተፈጠረውን ግጭት በአንቺም ተይ ፤ አንቺም ተይ ማስቆማቸው ይነገራል፡፡


ለዚህም የፓኪስታን መንግስት ሰሞኑን ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት እጩዬ ይሁኑልኝ ብሎ እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡


አሜሪካ በእስራኤል ተደረቢነት ኢራንን መምታት ጀምራለች፡፡


የፓኪስታን መንግስትም የአሜሪካን የኢራን ድብደባ ለማውገዝ እንዳላረፈደ ተጠቅሷል፡፡



የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሊባኖስ የሚገኙ የኤምባሲ እና የቆንስላ ፅኅፈት ቤት አብዛኞቹ ሰራተኞቹ ከዚያ ለቅቀው እንዲወጡ አዟቸዋል፡፡


ሌሎች አሜሪካውያንም ሊባኖስን ለቅቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡


አሳሳቢ የደህንነት ሁኔታ ለውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ትዕዛዝ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡


ቀደም ሲል እስራኤል በሔዝቦላህ ላይ ከፍታው በነበረ የጦር ዘመቻ ወቅት በሊባኖስ የነበሩ አሜሪካውያን ለቅቀው እንዲወጡ ታዝዘው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡


ዘግይቶ ግን ትዕዛዙ እንዲነሳ ተደርጎ ነበር ተብሏል፡፡


አሜሪካ በእስራኤል ተደራቢነት ኢራንን በጦር መምታት መጀመሯ ይታወቃል፡፡


የአሜሪካ ዜጎች ሊባኖስን ለቅቀው እንዲወጡ በየግል የኤሌክትሮኒክስ የመልዕክት አድራሻቸው /ኢሜይል/ ትዕዛዙ እንደተላለፈላቸው ታውቋል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page