ሰኔ 14 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- Jun 21
- 2 min read
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቺ እስራኤል በአገራችን ላይ የከፈተችውን ጥቃት ካላቆመች በፍጹም ወደ ኒኩሊየር ነኩ ድርድር በጭራሽ አንመለስም አሉ፡፡
አባስ አርጋቺ የአገራቸውን አቋም እወቁልን ያሉት በዚሁ ጉዳይ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከአውሮፓ አገሮች አቻዎቻቸው ጋር በተነጋገሩበት ወቅት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
አውሮፓውያኑ ኢራን ከአሜሪካ ጋር ቀደም ሲል ከአሜሪካ ጋር ኒኩሊየር ነኩን ድርድር እንድትቀጥል አርጋቺን አበክረው ጠይቀዋቸዋል፡፡
እስራኤል እና ኢራን ትናንት ሌሊቱንም አንዷ በሌላዋ ላይ ከበድ ከበድ ያሉ ጥቃችን መሰንዘራቸው ተሰምቷል፡፡

የእስራኤል ጦር በኢራን የሚሳየል ማከማቻዎች እና መተኮሻዎችን ዒላማ ያደረጉ ድብደባዎችን ፈፅሜያለሁ ብሏል፡፡
በኢራንም የሚሳየል ድብደባ በቴል አቪቭ አቅራቢያ ከፍተኛ ፍንዳታ ተሰምቷል መባሉ ተጠቅሷል፡፡
የእስራኤለ ጦር ኤታ ማጆር ሹም ኢያል ዛሚር አገራቸው ከኢራን ጋር በጀመረችው ግጭት ለተራዘመ ዘመቻ ዝግጁ መሆኗን እንደተናገሩ መረጃው አስታውሷል፡፡
የኒጀር ወታደራዊ መንግስት በፈረንሳዊ ኩባንያ ባለቤትነት ስር የሚገኝን የዩራኒየም ማዕድን ማምረቻ ወደ ብሔራዊ ሐብትነት አዞረዋለሁ አለ፡፡
በኒጀር ወታደራዊ መንግስት ተወርሶ ወደ ብሔራዊ ሀብትነት የሚዞረው ሶሚየር በተባለው ፈረንሳዊ ኩባንያ ባለቤትነት ስር ሲተዳደር የቆየ የዩራኒየም ማምረቻ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
መንግስት የማዕድን ኩባንያውን የሚወርሰው ያልተገቡ ተግባራትን እየፈፀመ ነው በሚል ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡
በኒጀር የጦር አለቆች በመንግስት ግልበጣ ስልጣን ከያዙ ወዲህ አገሪቱ ከቀድሞዋ ቅኝ ገዢዋ ጋር ያላትን ግንኙነት በእጅጉ እየደፈረሰ መምጣቱ ይነገራል፡፡
ኒጀር በቀጠናው ሰፍረው የነበሩ የፈረንሳይ ወታደሮችን ሙሉ በሙሉ ካስወጡት መካከል አንዷ ነች፡፡
ምእራብ አፍሪካዊቱ ኒጀር በአለም ላይ ከከፍተኛ የዩራኒየም ማዕድን መገኛዎች አንዷ እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡
ዩራኒየም ለኒኩሊየር የኤሌክትሪክ ማመንጫ እና በከፍተኛ ደረጃ የተብላላው ደግሞ ለኒኩሊየር ቦምብ መስሪያነት ይውላል፡፡
የየመን ሁቲዎች አሜሪካ በእስራኤል ተደራቢነት ኢራን በጦር የምትመታ ከሆነ እኛም ጥቃታችንን እንቀጥላለን ሲሉ ዛቱ፡፡
ሁቲዎቹ በቀይ ባህር ተላላፊ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ያቆሙት ከአሜሪካ ጋር በደረሱት የተኩስ አቁም እንደነበር አልጀዚራ አስታውሷል፡፡
የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ ከኢራን በተጓዳኝ እኛም በእስራኤል ላይ ሮኬቶችን እየተኮስንባት ነው ብለዋል፡፡
ሁቲዎቹ ቀደም ሲል የእስራኤል እና የአጋሮቿ ናቸው ባሏቸው የቀይ ባሕር ተላላፊ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ የቆዩት ለጋዛ ፍልስጤማውያን አጋርነታቸው ለማሳየት አልመው ነው ይባላል፡፡
የሁቲ ታጣቂዎች ሁነኞቹ የኢራን የጦር እና የፖለቲካ አጋሮች መሆናቸው ይነገራል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments