top of page

ሰኔ 14፣ 2016 - የኢትዮጵያን የግብርና ውጤቶች የሚገዙ ሀገራት በወረቀት የሚሰጠውን የምርቶቹን የጥራት እና ቁጥጥር ማረጋገጫ አንቀበልም እያሉ ስለመሆናቸው ተነገረ

የኢትዮጵያን የግብርና ውጤቶች የሚገዙ ሀገራት በወረቀት የሚሰጠውን የምርቶቹን የጥራት እና ቁጥጥር ማረጋገጫ አንቀበልም እያሉ ስለመሆናቸው ተነገረ።


በዚሁ ምክንያት ማረጋገጫውን የሚሰጠው የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን አሰራሩ ወደ ዲጂታል መቀየሩን ሠምተናል።


ይህንነኑ የተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።


ኢትዮጵያ አብዛኛውን የውጪ ምንዛሪ የምታገኘው ከግብርና ምርቶች ነው።


ቡናን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶች ከሚገኘው የውጪ ምንዛሪ እስከ 80 በመቶውን ለሀገር እንደሚያመጡ ይነገራል።


አሁን አሁን ግን ገዥ አገራት በእነዚህ የግብርና ምርቶች ላይ የቁጥጥር ስርአታቸውን እየቀያየሩ እና እያጠበቁ ናቸው ሲሉ፤የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ነግረውናል።


በዚህ ምክንያት የምርቶቹን የጥራት እና ደህንነት የማረጋገጥ ሃላፊነት የተሰጠው ባለስልጣን መስሪያ ቤታቸው፤ ከመስፈርቱ ጋር የሚሄድ አሰራር መከተል ግድ እንዳለው ጠቅሰዋል።


የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዳለ ሃብታሙም በተለይ የአውሮፓ ገዢዎቻችን፤ ጫካ እየጨፈጨፋችሁ የምታመጡትን የግብርና ምርት አንገዛም ፤ ከሶስት ዓመት በኋላ ደግሞ የኬሚካል አጠቃቀማችሁን በግማሽ ካልቀነሳችሁ ተመሳሳይ እርምጃ እንወስዳለን በማለት እያስጠነቀቁን ነው ሲሉ ነግረውናል።


ገዥ ሀገራት የቁጥጥር ስርአታቸውን ሲያጠብቁ አብረው የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ፤ በወረቀት የሚሰጠውን የግብርና ምርቶች የጥራት እና ደህንነት ማረጋገጫ አንቀበልም ማለታቸውን ሠምተናል።


መስሪያ ቤቱም አሰራሩን ዲጂታል ለማድረግ መወሰኑን ዋና ዳይሬክተሩ አምባሳደር ድሪባ ኩማ ተናግረዋል።


በአዲሱ አሰራር ዙሪያም በሃይሌ ግራንድ ሆቴል በተዘጋጀ ውይይት ላይ የሚመለከታቸው ሀሳብ እንዲሰጡ ተደርጓል።


የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ውይይቱን ያዘጋጀው ከኢትዮጵያ አበባ፤ አትክልት፤ ፍራፍሬ ፤ ስራ ስር እና መዓዛማ ውጤቶች አምራቾችና ላኪዎች ማህበር እና ኢግናይት ኮንሰለት ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር እንደሆነ ሠምተናል።


ንጋቱ ረጋሣ



留言


bottom of page