top of page

ሰኔ 14፣ 2016 - አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የተረጋገጡ ቁጥራዊ መረጃዎች ባለመኖራቸው የአካል መደገፊያ ስርጭት ላይ ተጽዕኖ እየተፈጠረ ነው ተባለ

አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ከግምት ባሻገር የተረጋገጡ ቁጥራዊ መረጃዎች ባለመኖራቸው የአካል መደገፊያ ስርጭት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየተፈጠረ ነው ተባለ።


በመረጃ ክፍተቱ ምክንያት አንዴ እንኳን መደገፊያውን ያላገኙ አካል ጉዳተኞች እያሉ ሁለቴ የሚወስዱ እንዳሉ ተነግሯል።


የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ቀድሞ በተናጠል ይሰሩ የነበሩ ሶስት ተቋማት ማለትም የኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ ድርጅት፣ የማህበረሰብ ልማት ማሰልጠኛ ተቋም እና ገፈርሳ የአዕምሮ ተሀደሶ ህክምና መስጫ ማዕከል በአንድ በማዋኸድ በ2014 ዓ.ም በአዋጅ የተቋቋመ ነው፡፡


ተቋሙ እንደ ክራንች፣ ዊልቸር፣ ሰው ሰራሽ እጅ እና እግር እንዲሁም መሰል የአካል መደገፈያዎችን አምርቶ ለሚያስፈለጋቸው በነጻ እና ከገበያ ዋጋ ባነሰ ዋጋ የማቅረብ ሀላፊነትም ተሰጥቶታል፡፡


ሸገር ተቋሙ ባለፉት 2 ዓመታት ምን ሰራ፤ አሁንስ ምን እየሰራ ይገኛል? ሲል ጠይቋል፡፡


ጉዳት ለደረሰባቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አካል ጉዳተኞች የአካል መደገፊያ እያቀረበ እንደሆነ ተቋሙ ለሸገር ተናግሯል፡፡


ነገር ግን አቀርቦቱ ከሚፈለገው አንጻር በቂ የሚባል አይደለምም ተብሏል፡፡


ለዚህም የመረጃ ክፍተት፣ የሰው ሀብት እና የግብዓት እጥረት ችግር እንደሆኑ ተነግሯል፡፡


በተቋሙ የተሀድሶ ህክምና ባለሞያ ፀጋዬ ፎንዢየ፤ የአካል መደገፊያ ለመስራት የሚያገለግሉ ግብዓቶች ዉድ በመሆናቸው፤ ተቋሙ የአካል መደገፊያን በበዛት ለማምርት እየቻለ አይደለም ብለውናል፡፡

አካል ጉዳተኞች በተመለከተ ከግምት ባሻገር የተረጋገጠ ቁጥራዊ መረጃዎች በሀገሪቱ አለመኖሩ የተቋሙ ስራ ላይም ተፅእኖ እያደረገ ነውም ተብሏል፡፡


በዚህ የመረጃ ክፍተት ምክንያትም ለአንዳንድ አካባቢ ያሉ አካል ጉዳተኞች አንዴም ድጋፍ ያላገኙ እያሉ በሌሎች አካባቢዎች ድግሞ ሁለቴ የሚሰጣቸው መኖራቸውንም አቶ ፀጋዬ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት የቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በየትምህርት ቤቱ በሱስ የተያዙ ተማሪዎችን ከገቡበት ሱስ የማላቀቅ ስራ ጀምሬአለሁም ብሏል፡፡


ጉለሌ ፋና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እና አስኮ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በርትቼ መስራት ከጀመርኩባቸው ትምህርት ቤቶች የምጠቅሳቸው ናቸው ሲል ተቋሙ ለሸገር ተናግሯል፡፡



ማንያዘዋል ጌታሁን ያሰናዳውን በምንታምር ፀጋው

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page