top of page

ሰኔ 14፣ 2016 - አንዳንድ የውጭ ባለሃብቶች በተሳሳተ መረጃ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ለቀው እየሄዱ ነው ተብሏል

አንዳንድ የውጭ ባለሃብቶች በተሳሳተ መረጃ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ለቀው እየሄዱ ነው ሲል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ተናገረ።


በዚህም ምክንያት ሁሉንም ችግር ተጋፍጠው የሚሰሩ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለመሳብ እና በሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ በሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲሸፈን የተለያዩ የአሠራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውም ተነግሯል።


የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ በሀገሪቱ አንዳንድ ችግሮች ሲከሰቱ የውጭ ባለሀብቶች በትዕግስት ነገሮችን ከማየት እና ትክክለኛውን መረጃ ከማጣራት ይልቅ በተሳሳተ መረጃ ከዘርፉ በቶሎ ይወጣሉ ብለዋል።


የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ግን ችግሮች ቢከሰቱም ስራቸውን በፅናት ስለሚቀጥሉ ለሀገር ውስጥ ባለሃብት ትኩረት እንድናደርግ ምክንያት ከሆኑን ውስጥ አንዱ ነው ሲሉ ነግረውናል።


የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ወደ ኢንቨስትመንት ገብተው መዋዕለ ነዋያቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ ለማበረታታት የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎችን አድርገናል የሚሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ከተደረጉ ማሻሻያዎች የታሪፍ ማሻሻያ እና የመሬት ኪራይ ክፍያ አንዱ ነው ብለዋል።


ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ አክሊሉ ታደሰ አክለውም የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታትም በአገር ውስጥ የሚመረት ምርት ከውጪ እንዳይገባና ከሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲገዛ መወሰኑንም ተናግረዋል።


በኢትዮጵያ አሁን ላይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚገኙ ኢንቨስተሮች ውስጥ 55 በመቶው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መሆናቸውንም ሰምተናል።



コメント


bottom of page