top of page

ሰኔ 13፣ 2016 በመጠናቀቅ ላይ ያለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በጉባ አካባቢ ያለውን ሞቃት የአየር ጠባይ እየቀየረው መጥቷል ተባለ

  • sheger1021fm
  • Jun 20, 2024
  • 1 min read

በመጠናቀቅ ላይ ያለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በጉባ አካባቢ ያለውን ሞቃት የአየር ጠባይ እየቀየረው መጥቷል ተባለ፡፡


በከፍተኛ የሙቀት መጠን የሚታወቀው የህዳሴ ግድብ እየተገነባበት ያለው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚገኘው የጉባ አካባቢ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአየር ጠባዩ እየተቀየረ፣ የነበረው ከባድ ሙቀት መቀነስ አሳይቷል ተብሏል፡፡


ይህ የተባለው ከሰሞኑ በግድቡ ግንባታ ወቅት መገናኛ ብዙሃን የነበራቸውን ሚና በተመለከተ ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው፡፡


በዚህም ወቅት የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት እንዳለው በግድቡ ስራ ምክንያት የጉባ አካባቢ ስነ ምህዳር ተቀይሯል፤ ምድረ በዳ የነበረው ስፍራው ለኑሮ ምቹ ወደ መሆን እየተሸጋገረ፤ አንዳንድ ጊዜም ለመተንፈስ እንኳን አስቸጋሪ የነበረው የሙቀት መጠን እተስተካከለ ነው ተብሏል፡፡


በሺዎች የሚቆጠሩ የግድቡ ሰራተኞች አስቸጋሪውን የአካባቢውን ሙቀት ተቋቁመው እንደሚሰሩ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲነገር ሰምተናል፡፡


በተለይም ግድቡ በተጀመረበት ወቅት የሙቀት መጠኑ ከ45 እስከ 52 ዲግሪ ሴልሲየስ የሚደርስ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡


ያ ንዳድ የሆነ ሙቀት አሁን ቀንሷል እየተባለ ነው፡፡


በእርጥም የጉባ የአየር ሁኔታ መስተካከል አሳይቷል? የሚለውን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲን ጠይቀናል፡፡


በኤጀንሲው የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ሃላፊ የሆኑት አሳምነው ተሾመ(ዶ/ር) በጉባ አካባቢ ያለው የሙቀት መጠን ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ ከከፍተኛ ወደ መካከለኛ መምጣቱን አረጋግጠውልናል፡፡


ባለሞያው እንደሚሉት ባለፈው የበልግ ወቅት የጉባ ሙቀት እስከ 33 ዲግሪ ሴልሺየስ የደረሰ ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ይህ ቀንሶ እስከ 28 ዲግሪ ሴልሺየስ ሆኗል፡፡


በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የግድቡ ግንባታ ከዚህ በኋላ ያለው ስራ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የመጠበቅና፣ የአካባቢውን ስነ ምህዳር አስጠብቆ እንዲዘልቅ ማድረግ ደግሞ ከዚህ ትውልድ እንደሚጠበቅ የነገሩን ደግሞ በማስተባበሪያ ምክር ቤቱ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ አለባቸው ሙላት ናቸው፡፡


በጉባም ይሁን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመጪዎቹ ቀናት እንደ ተቀረው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን እንደሚኖረውም ባለሞያው ጠቁመዋል፡፡


ምንታምር ፀጋው

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page