top of page

ሰኔ 12 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች - እስራኤል፣ ኢራን እና አሜሪካ

  • sheger1021fm
  • Jun 19
  • 2 min read

እስራኤል እና ኢራን አንዷ በሌላዋ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል ተባለ፡፡


እንደሚባለው የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአገራቸው በእስራኤል ተደራቢነት ኢራንን የምትመታበትን ጉዳይ እያጤኑት ነው፡፡


ትራምፕ በዚሁ ጉዳይ እቅጩን እንዲናገሩ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ላደርገውም ፤ ላላደርገውም እችላለሁ የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ኢራንን ማስደብደባቸው አይቀሬ እንደሆነ CBS ፅፏል፡፡


የሚጠብቁት ነገር ምናልባት የኢራን መሪዎች በቃ የኒኩሊየር መርሐ ግብራችንን ትተነዋል ተውን እስኪሏቸው መሆኑ ተገምቷል፡፡


በዚህም የተነሳ ቁርጥ ካለው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አልደረሱም ተብሏል፡፡


የፋርስ ባሕረ ሰላጤው ግጭት በተባባሰበት በአሁኑ ወቅት የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ለነገ ቀጠሮ መያዙ ተሰምቷል፡፡

የምክር ቤቱ ስብሰባ የተጠራው በኢራን ጥያቄ መሆኑ ታውቋል፡፡


ቻይና ፣ ሩሲያ እና ፓኪስታን ደግሞ የስብሰባው መጠራት ደጋፊዎች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡



ኢራን የእስራኤሏ ሐይፋ ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ ለቅቀው እንዲወጡ አስጠነቀቀች፡፡


ማስጠንቀቂያው በኢራኑ መንግስታዊ ቴሌቪዥን አማካይነት መነገሩን ዲፌንስ ፖስት ፅፏል፡፡


በመንግስታዊው ቴሌቪዥን የተላለፈው ማስጠንቀቂያ የሐይፋ ነዋሪዎች ለራሳቸው ደህንነት ሲባል ለቅቀው እንዲወጡ ጠይቋል፡፡


ማስጠንቀቂያችንን ቸል ካላችው የሚሳየላችን ሲሳይ ትሆናላችሁ ብሏቸዋል፡፡

በሌላ መረጃ ኢራን በደቡባዊ እስራኤል በአንድ ሆስፒታል ላይ በፈመችው ድብደባ በአንድ ሆስፒታል እና በአቅራቢያው ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ሹሞች ተናግረዋል፡፡


በኢየሩሳሌም ከባድ ፍንዳታ መሰማቱን AFP ፅፏል፡፡


በኢራን ደግሞ የኢንተርኔት (መረጃ መረብ) አገልግሎቱ በአብዛኛው አገልግሎት መስጠት ከማይችልበት ደረጃ መድረሱን የፃፈው ደግሞ ዴይሊ ኒውስ ነው፡፡



አሜሪካ ታላላቅ የጦር መርከቦቿን በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ቦታ ቦታቸውን እያስያዘቻቸው ነው ተባለ፡፡


የጦር መርከቦቹ ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ፣ ወደ ሆርሙዝ እና የሳታላይት ምስሎች ማሳየታቸው አናዶሉ ፅፏል፡፡


ሰኞ እለት ከአሜሪካ ታላላቅ የጦር መርከቦች መካከል ኒሚትዝ የተባለችዋ ከደቡብ ቻይና ባሕር ወደ መካከለኛው ምስራቅ አምርታለች ተብሏል፡፡


አሜሪካ በአውሮፓ ያሉ ነዳጅ በአየር ላይ የሚያቀብሉ አውሮፕላኖቿን እያዘጋጀች ነው መባሉ ተሰምቷል፡፡


የአሜሪካ የጦር ሹሞች ዝግጅታችን ለመከላከል እንጂ ለማጥቃት የታለመ አይደለም ሲሉ ሰንብተዋል፡፡


ያም ሆኖ አሜሪካ በእስራኤል ተደራቢነት ኢራንን ልትመታ ትችላለች የሚለው ግምት ከሰዓት ሰዓት እያየለ መምጣቱ ይነገራል፡፡



በደቡባዊ እስራኤል የሚገኝ ሆስፒታል የተመታው የአቅራቢያውን ወታደራዊ ተቋም ዒላማ አድርጎ እንደነበር የኢራን የጦር ሹሞች ተናገሩ፡፡


በእስራኤል ቢርሼቫ የሚገኝ ሆስፒታል ኢራን በተኮሰችው ሚሳየል ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ቢቢሲ አስታውሷል፡፡


የኢራን ጦር ሆስፒታሉ ዒላማዬ አልነበረም ማለቱን የኢራን መገናኛ ብዙሃን አውርተዋል፡፡


በሆስፒታሉ አቅራቢያ የእስራኤል ከፍተኛ የጦር ትምህርት ቤት እንደሚገኝ ይነገራል፡፡


ከ30 ያላነሱ ሰዎች ጉዳት እንደገጠማቸው ተሰምቷል፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ አምባገነኖች ሲሉ የጠሯቸው የኢራን መሪዎች በሆስፒታሉ ላይ ለተፈፀመው ጥቃት የእጃቸውን ያገኛሉ ሲሉ መዛታቸው ተሰምቷል፡፡


ሆስፒታሉ ከተመታ በኋላ አስተዳዳሪዎቹ ሕሙማን የኬሚካል መመረዝ ሊገጥማቸው ስለሚችል እንዳይመጡባቸው ጠይቀዋል፡፡


ሆስፒታሉ አብዛኞቹን ተኝቶ ታካሚዎች ከአደጋ ወደሚጠበቁበት ምድር ቤት ካሸጋገራቸው መሰንበቱን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page