የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአንድ ጊዜ ከ 30.01 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለሚያቀርቡልኝ አቅራቢዎች በዓለም ገበያ ዋጋ ላይ 72 በመቶ ማበረታቻ ጭማሪ እያደረኩ እገዛለሁ ሲል ተናገረ።
ባንኩ ከ 3.01 ኪሎ ግራም ጀምሮ እስከ 30 ኪሎ ግራም ወርቅ ለሚያቀርቡልኝ አቅራቢዎች ደግሞ በዓለም ገበያ ዋጋ ላይ 67 በመቶ ማበረታቻ ተጨማሪ እየተደረገላቸው ግዢው ይፈጸማል ብሏል።
በተመሳሳይ በአንድ ግዜ ከ 50 ግራም ጀምሮ እስከ 3 ኪሎ ግራም ወርቅ አቅራቢዎችም 60 በመቶ በዓለም ገበያ ዋጋ ግዢው እንደሚፈፀም ብሔራዊ ባንኩ ወስኗል።
ይህ ማሻሻያ ከሰኔ 10 ቀን 2016ዓ ም ጀምሮ የሚፈፀም ነው ተብሏል።
በማዕከል እና ክልሎች በሚገኙ የወርቅ ግዥ ማዕከላት በኩል የሚገዛውን ወርቅ ዋጋ ላይ ማሻሻያ የተደረገው የወርቅ ምርት ላይ በርካታ ችግሮች በመኖራቸው መሆኑን ሰምተናል።
ኢትዮጵያም ማግኘት የነበረባትን የውጭ ምንዛሪ እና ሌሎች ከዘርፉ የሚጠበቁ በርካታ ገቢዎች ከሚጠበቀው በታች እየወረዱ መምጣታቸውም ታውቋል።
ለወርቅ አቅራቢዎች የሚከፈለው ማበረታቻ ተወዳዳሪ ባለመሆኑም ለባንኩ መቅረብ የነበረበት ወርቅ በሕገ ወጥ መንገድ በኮንትሮባንድ ገበያ እንዲሸጥ ምክንያት መሆኑን ብሔራዊ ባንክ አረጋግጫለሁ ብሏል።
በመሆኑም፣ ለወርቅ አቅራቢዎች የተሻለ የዋጋ ማበረታች በመስጠት እና አቅርቦትን ለመጨመር መመሪያ ተሻሽሏል ተብሏል።
ከወርቅ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ከፍ ለማድረግ ከባሀላዊ የወርቅ ዘርፍ የሚገኘውንም የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ በስራ ላይ ያለውን የወርቅ ዋጋ ማበረታች ማሻሻሉን ማእከላዊ ባንኩ ከላከልን ከላከልን ማስረጃ ተመለክተናል።
በተያያዘ የማዕድን ሚኒስቴር ከ2010 እስከ 2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 4.2 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ አቅዶ መስብሰብ የቻለዉ 1.2 ቢሊዮን ብቻ ነዉ ተብሏል፡፡
በዘንድሮ 2016 የመጀመርያው ሩብ ዓመት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ወርቅ በሀገር እየተመረተ ቢሆንም ወርቂቱን የመግዛት ብቸኛ ሥልጣን ለተሰጠው ብሔራዊ ባንክ እየቀረበ ያለው መጠን ትርጉም ባለው ሁኔታ ቀንሷል ማለታቸው ይታወሳል።
ከዓመታት በፊት ኢትዮዽያ ከወርቅ ኤክስፖርት ብቻ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታገኝ የነበር ሲሆን አሁን ግን ማሽቆልቆሉ ይታወቃል።
በተያያዘ ወሬ የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ በዘንድሮ ሩብ ዓመት ከወርቅ ሽያጭ የተጠበቀው ገቢ ከ112 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፣ ነገር ግን የተገኘው እንደ እቅዱ አይደለም በጣም ትንሽ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ተህቦ ንጉሴ
Komentáře