top of page

ሰኔ 11፣ 2016 - 2 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩ ተጨማሪ 5 የህዳሴ ግድብ ተርባይኖች ወደ ስራ ይገባሉ ተባለ

የግንባታ ስራው 96 በመቶ የደረሰው የህዳሴ ግድቡ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል ሁለቱ ተርባይኖች በአማካኝ 540 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጩ መሆኑን ሸገር ሰምቷል።


የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ኃይሉ አብርሃም ለሸገር እንዳሉት 5ቱ ተርባይኖች በቅርቡ ሃይል ማመንጨት ይጀምራሉ።


የግድቡን 4 በመቶ ቀሪ ስራ ለማጠናቀቅ 45 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሃይሉ በዚህ ዓመት 10 ወራት 1.2 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል ብለዋል።


በአጠቃላይ በ13ቱ ዓመታትም ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ከህዝቡ የተሰበሰበ ሲሆን ይህም ከሚያስፈልገው 10 በመቶው መሆኑንም አስረድተዋል።


ቀሪው 90 በመቶ ከመንግስት ካዝና እየወጣ እንደተሰራም ተነግሯል።


በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመግዛት ጥያቄ ላቀረቡ ለጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ የመስመር ዝርጋታ እየተከናወነ መሆኑንም ሃላፊው ጠቁመውናል።


የህዳሴ ግድቡ ያሉት 13 ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 4 መቶ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ መሆናቸውንም ከሃላፊው ሰምተናል።

ምንታምር ፀጋው

Commentaires


bottom of page