top of page

ሰኔ 11፣ 2016 - አንድ ሰው የአዕምሮ ህመም ገጥሞት ወደቀደመው ህይወቱ እንዲመለስ የሚደረገው የተሀድሶ ህክምና በኢትዮጵያ እጅግ ዝቅተኛ ነው ተባለ

አንድ ሰው የአዕምሮ ህመም ገጥሞት ወደቀደመው ህይወቱ እንዲመለስ የሚደረገው የተሀድሶ ወይም ሪሀቢሊቴሽን ህክምና በኢትዮጵያ እጅግ ዝቅተኛ ነው ተባለ፡፡


በጤናው ዘርፍ በአብዛኛው ቅድሚያ የሚሰጣቸው በዓይን ለሚታዩና በአካል ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ህክምና እንጂ የአዕምሮ ህመም ህክምና እና የተሀድሶ አገልግሎቱ ብዙም አልተሰራበትም የሚሉት የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም ናቸው፡፡


በአዕምሮ የተሐድሶ ህክምና አገልግሎት ከሰዎች የአኗኗር ፣ማህበራዊ ግንኙነት እና የዕለት ተዕለት ተግባቦት አንጻር የሚሰጡ መሆናቸውንና የአዕምሮ ህመም ይህንን የሰዎች ክህሎት የሚያሳጣ መሆኑንም ፕሮፌሰር አታላይ ተናግረዋል፡፡


የአዕምሮ የተሀድሶ ህክምና ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ ለህመሙ መፍትኤ የሚሰጥና ከሌሎች በመድሃኒት መልክ ከሚሰጡ ያነሰ ዋጋ እና የተሸለ የህክምና ሥርዓት በመሆኑ ማዕከላቱን በማስፋፋት እና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተብሏል፡፡


በዓለም ላይ አንድ ቢሊየን ያህል ሰዎች የተለያየ ዓይነት የአዕምሮ ህመም እንዳለባቸው የተነገረ ሲሆን ነገር ግን የአዕምሮ ጤና ጉዳይ የአንገብጋቢነቱን ያህል በሀገራት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን የአለም የጤና ድርጅት ሪፖርት ያሳያል፡፡


ምህረት ስዩም



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Comments


bottom of page