ሰኔ 10፣ 2016 - በአዲስ አበባ በመጪው የትምህርት ዘመን 82 የግል ትምህርት ቤቶች እንደማያስተምሩ ተነገረ
- sheger1021fm
- Jun 17, 2024
- 1 min read
ከ82ቱ ትምህርት ቤቶች መካከል የአፍ መፍቻ ቋንቋን ባለማስተማር እና በመሰል የፖሊሲ ጥሰት 40 የግል ት/ቤቶች እግድ እንደተጣለባቸው የአዲስ አበባ የትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥር ባለስልጣን ተናግሯል፡፡
ብዙዎቹ ቅድመ አንደኛ እና አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ናቸው ተብሏል፡፡
ቀሪዎቹ ደግሞ በራሳቸው ፈቃዳቸውን የመለሱ ናቸው ብሏል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ዳኛው ገብሩ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት እግድ የተጣለባቸው ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ባለማስተማራቸውና የወጣውን የሀገሪቱ ትምህርት ስርአት ባለማክበራቸው ነው።
እግድ የተጣለባቸው 35ቱ ቅድመ አንደኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርትቤቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤቶች ናቸው ተብሏል።
በቅርቡ ከአዲስ አበባ ትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር ችግሬን ፈትቼ ነበር ያለው ጊብሰን ትምህርት ቤትንም ጨምሮ ቅዱስ ሚካኤል ትምህርት ቤቶች ፍቃዳቸውን ከተነጠቁ ትምህርት ቤቶች መካከል ናቸው።
ቅዱስ ሚካኤል ዳግም ስራ ለመጀመር እንደ አዲስ ለመመዝገብ ጥያቄ ማቅረቡና ባለስልጣኑም እየተመለከተው እንደሆነ የተናገሩት ዋና ስራ አስኪያጁ ሌሎቹ ግን ከዚህ በኋላ ለ2017 የትምህርት ዘመን እንደ አዲስ መመዝገብ አይችሉም ተብሏል።
ፍቃዳቸው በትነሳባቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች በፈለጉት ትምህርትቤት መመዝገብና ትምህርታቸውን መቀጠል ይችላሉ ሲል ባለስልጣኑ ተናግሯል።
አዲስ አበባ ውስጥ 2110 ከቅድመ አንደኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን 1559 የሚሆኑት የግል ትምህርት ቤቶች ናቸው።
ከእነዚህ ውስጥ ለ2017 የትምህርት ዘመን ፍቃዳቸው ያደሱት 1332 ትምህርት ቤቶች ናቸው መባሉን ሰምተናል።
ወላጆች ልጆቻቸውን ፍቃዳቸው በተነጠቁ ትምህርት ቤቶች እንዳያስመዘግቡ ሲል አሳስቧል።
ጊብሰን ትምህርት ቤት ከንቲባ አደነች አበቤ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ባለስልጣኑ ተወያይተው ችግሩን ለመፍታት ስምምነት ላይ ቢደረስም ትምህርት ቤቱ ግን የተሰጠውን እድል አልተጠቀመበትም ብለዋል ሀላፊው በመግለጫው።
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Comments