ሰኔ 1፣2016 - አካባቢን ይበክሉ የነበሩ ስድስት የመንግስት ተቋማት የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ውሳኔ ተላልፏል ተባለ
- sheger1021fm
- Jun 8, 2024
- 1 min read
በጎ ፈቃደኞች ህዝብን ወክለው በከወኑት ስራ፤ አካባቢን ይበክሉ የነበሩ ስድስት የመንግስት ተቋማት የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ውሳኔ ተላልፏል ተባለ፡፡
የአካባቢ ብክለትን አስከትለዋል የተባሉ እንደ ቄራ እና የቁም እንስሳት መሸጫ ያሉትን ጨምሮ በአዲስ አበባና በሐዋሳ ያሉ መንግስታዊ ተቋማት ላይ ህዝብን ወክለው ክስ በመመስረት በፍርድ ቤት ችግሩ እልባት እንዲያገኝ አስችሏል የተባለው ‘’ቁም ለአካባቢ’’ የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡
ህዝብ ደህንነቱ በተጠበቀ አካባቢ የመኖር ህገ መንግስታዊ መብቱ እንዲከበር ተቋሙ እየሰራ ያለውም በበጎ ፈቃደኞች እገዛ መሆኑን የቁም ለአካባቢ መስራች እና የቦርድ ሰብሰቢ አቶ መልካሙ ኦጎ ለሸገር ተናግረዋል፡፡

እስካሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ መንግስታዊ ተቋማት አካባቢን ከሚበክል ስራቸው እንዲቆጠቡ የተለያዩ ውሳኔዎች እንዲተላለፉባቸው አንዳንዶቹም ችግሩን አምነው በራሳቸው እንዲያስተካክሉ ማድረግ ችለናል ብለዋል፡፡
በዚህ ስራም በጎ ፈቃደኛ ጠበቃና የህግ አማካሪዎች ጉዳዩን ፍርድ ቤት ውሰዶ በመከራከር፣ የጤና ባለሞያዎች እና ሌሎች ደግሞ የቁም ለአካባቢ ስራ የሰመረ እንዲሆን ጥናቶችን በማካሄድ በበጎ ፈቃድ እየሰሩ ነው ተብሏል፡፡
ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሚደረግን የበጎ ፈቃድ ስራ ለማበርታት እንዲሁም ሰዎች ጤናማና እና ንፅህናው በተጠበቀ አካባቢ እንዲኖሩ ላበረከቱት ስራ ዛሬ ለ41 በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች በአዲስ አበባ እውቅና ተሰጥቷቸዋል ብለዋል አቶ መልካሙ፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
Comments