top of page

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጦርነት ጉዳይ ''ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ንትርክ ውስጥ መግባት ባልሻም በጦርነት አውጋዥነቴ ግን እገፋበታለሁ'' አሉ፡፡

  • Apr 14
  • 2 min read

ሚያዝያ 6/2018 - ዓለም አቀፍ ወሬዎች

 

 

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጦርነት ጉዳይ ከአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ንትርክ ውስጥ መግባት ባልሻም በጦርነት አውጋዥነቴ ግን እገፋበታለሁ አሉ፡፡

 

ቀደም ሲል ትራምፕ የካቶሊኩን ርዕሠ ጳጳስ ደካማ ሲሉ መጥራታቸውን አናዶሉ አስታውሷል፡፡

 

ሊዮ 14ኛ በአልጀሪ ጉብኝታቸው ወቅት ትራምፕ ያሻቸውን ቢሉም ጦርነትን በብርቱ ማውገዜን እገፋበታለሁ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡



እኔ የወንጌል ሰባኪ ነኝ በአለም ሰላም እንዲሰፍን ከመናገር ወደ ኋላ አልልም ብለዋል፡፡

 

ትራምፕ ቀደም ሲል ኢራን የኒኩሊር የጦር መሳሪያ ባለቤት መሆኗን የሚደግፍ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አልፈልግም ማለታቸው መረጃው አስታውሷል፡፡

 

አሜሪካ እና ኢራን በጠላትነት ከተሰለፉባቸው ጉዳዮች ዋነኛው የኒኩሊየር ጉዳይ መሆኑ ይነገራል፡፡

 

 

አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የኢራን የጦር ክፍል አለም አቀፍ የሆርሙዝን የባህር መተላለፊያን የመዝጋት የአሜሪካ እርምጃ አለም አቀፍ ወንጀል ነው አለው፡፡

 

የኢራን ጦር አስተያየት የተሰማው አሜሪካ ትናንት ከቀኑ 8 ሰዓት አንስቶ የሆርሙዝ የባህር መተላለፊያ ወሽመጥ ለመርከቦች ምልልስ ዝግ አድርጌዋለሁ ማለቷን ተከትሎ እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡

 

አሜሪካ ወሽመጡን ከመዝጋቷ በተጨማሪ በአቅራቢያው የኢራን ወደቦች መርከቦች እንዳይገቡም ሆነ እንዳይወጡ ከልክያለሁ ማለቷ ተሰምቷል፡፡

 

በፓኪስታን በሳምንቱ መጨረሻ የተካሄደው ድርድር ያለ ስምምነት ካበቃ በኋላ አሜሪካ በኢራን ላይ ጫናዋን እያበረታችባት ነው፡፡

የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የኢስላምአባዱ ንግግር የከሸፈው በአሜሪካ የማይጠረቃ ፍላጎት ምክንያት ነው ሲሉ አማረዋል፡፡

 

ኢራን የመጣውን እንደ አመጣጡ መክቼ እመልሳለሁ እያለች መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡

 

 

የእስራኤል መንግስት በዌስት ባንክ 34 አዳዲስ የአይሁዳውያን የሰፈራ መንደሮችን ለመገንባት የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉ ተሰማ፡፡

 

ውሳኔው የተላለፈው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቢሆንም ውሳኔው የታወቀው ዘግይቶ እንደሆነ ታይምስ ኦፍ ኢስራኤል ፅፏል፡፡

 

ዘግይተው የእስራኤሉ የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች በዌስት ባንክ የ33 አዳዲስ የአይሁዳውያን የሰፈራ መንደሮች ግንባታ ፈቃድ መሰጠቱን እንዳረጋገጡ የፃፈው ደግሞ ሚድል ኢስት ሞኒተር ነው፡፡

 

ቤዛሌል ስሞትሪች እርምጃው ታሪካዊ ሲሉ ጠርተውታል፡፡

 

በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ዌስት ባንክ የፍልስጤማውያን ይዞታ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

 

ባርናማ እንደፃፈው የአውሮፓ ህብረት የእስራኤልን መንግስት ህገ-ወጥ ብሎታል፡፡

 

የአረብ ሊግ ደግሞ ውሳኔውን እንዳወገዘው መረጃው አስታውሷል፡፡

 

 

በቤኒን በተካሄደው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ገዢውን የፖለቲካ ወገን የወከሉት ራሙአልድ ዋዳግኒ አሸነፉ ተባለ፡፡

 

የቅድሚያ ውጤቱ ዋዳግኒ ለፕሬዘዳንታዊ ምርጫው ከተሰጠው ድምፅ 94 በመቶውን ማግኘታቸውን እንደሚያሳይ አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡

 

የዋዳግኒ ዋነኛ ተፎካካሪ የነበሩት ግለሰብ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርጫ ውጤቱን ከማፅደቁ አስቀድሞ ሽንፈታቸውን መቀበላቸው ተሰምቷል፡፡

 

ዋዳጋኒ የተሰናባቹ ፕሬዘዳንት ፓትሪስ ታሎን ድጋፍ አልተለያቸውም ተብሏል፡፡

 

አገሪቱ ድህነት የተንሰራፋበት እንደሆነች ይነገራል፡፡

 

ከቅርብ አመታት ወዲህ የፅንፈኛ ታጣቂዎች ዒላማ እየሆነች መምጣቷን መረጃው አስታውሷል፡፡

 

 

ሰሜን ኮሪያ እጅግ ታላላቅ የጦር መሳሪያዎችን መሞከሯ ተሰማ፡፡

 

እስያዊቱ አገር ስትራተጂያዊ የረጅም ርቀት ተወንጫ የክሩዝ ሚሳል እና ፀረ ጦር መርከብ ሚሳየሎችን ለሙከራ መተኮሷን ስትሪየት ታይምስ ፅፏል፡፡

 

ሚሳየሎቹ አገሪቱ ሰርታ ለአገልግሎት ካበቃቻቸው ግዙፍ የጦር መርከቦች ከአንዱ መተኮሳቸው ታውቋል፡፡

 

ሙከራውን የአገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና ከፍተኛ የጦር እና የባህር ሀይል አዛዦች በቅርበት ተከታትለውታል ተብሏል፡፡

 

ስትራጂያዊ ክሩዝ ሚሳየሉ የኒኩሊየር ርዕሰ ጦር የሚገጠምለት እንደሆነ ታውቋል፡፡

 

ኪም ጆንግ ኡን ሙከራው ለስትራተጂያዊ መከላከያችን የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ እና ከአሜሪካ ጋር በቋሚ የጦር ፍጥጫ ላይ ትገኛለች፡፡

 

በዚህም የተነሳ የአዳዲስ የጦር መሳሪያዎች ፈጠራ እና ሙከራዋ በላይ በላዩ መሆኑ ይነገራል፡፡

 

የኔነህ ከበደ

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page