top of page

ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የ24 ምርጫ ክልሎች ዉጤት፤ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ እጩ ለፓርላማ አንዲሁም የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ እጩ ለክልል ም/ቤት ከፍተኛ ድምጽ አገኙ።

  • Jun 10
  • 2 min read

ሰኔ 3/2018


ምርጫ ቦርድ ትናንት ምሽት ላይ ይፋ ባደረገው የ24 ምርጫ ክልሎች ዉጤት፤ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ እጩ ለፓርላማ እንዲሁም የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ እጩ ለክልል ምክር ቤት ከፍተኛ ድምጽ አገኙ።


ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ለፓርላማ ወንበር ከፍተኛ ደምጽ ያገኙት ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን አቶ ጣሂር ሞሀመድ ሲሆኑ ለክልል ምክር ደግሞ የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ እጩው አቶ አሲል አርባብ ሃሚስ ናቸው።


ቦርዱ በትናንትናው እለት (ሰኔ 02 ቀን 2018 ዓ.ም) ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ በስካይ ላይት ሆቴል በአራት ክልሎች የ24 ምርጫ ክልሎችን ውጤት ተናግሯል።


በዚህም በኦሮሚያ ክልል የ8 የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልሎችን እና የ11 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ክልሎችን ውጤት ይፋ አድርጓል።

በኦሮሚያ ለክልል ምክር ቤት ድምጽ በተሰጠባቸው ጪሮ 2፣ ቀንበቢት፣ ሚጨታ፣ ጎማ 1፣ ሂርና፣ ጀልዱ፣ ግራዋ እና በዴሳ ምርጫ ክልሎች የብልፅግና ፓርቲ እጩዎች ከፍተኛ ደምጽ አግኝተዋል።


እንዲሁም ለ11 የፓርላማ ምርጫ ክልል (በጎማ 1፣ አርቦዬ፣ ሃሮማያ 1፣ ሳቡሬ፣ ጫንጮ ፣ ጪሮ 2፣ ዖሞ ናዳ 1፣ ሚጨታ፣ በዴሳ እና ውንጪ) ምርጫ ክልሎች የበልጽግና ፓርቲ እጩዎች ከፍተኛ ድምጽ እንዳገኙ ምርጫ ቦርድ ለጋዜጠኞች ይፋ አድርጓል።


ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአማራ ክልል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሁለት ምርጫ ክልሎችን እና የአንድ የክልል ምክር ቤት ውጤትንም አሳውቋል።


በዚህም መሰረት በጎንደር ዙሪያ 4 ምርጫ ክልል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የብልፅግና ፓርቲ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን እጩዎች ከፍተኛ ድምፅ አግኝተዋል ብሏል።


በክልሉ ይፋ ባደረገው አንድ የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልል ማለትም በመቄት 1 የብልፅግና ፓርቲ እጩዎች ከፍተኛ ደምጽ አግተዋል።


አንዲሁም በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም የአንዳንድ የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልሎችን ቦርዱ አሳውቋል።


በዚህም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩሙሩክ ምርጫ ክልል 8 የብልፅግና እጩዎች እና አንድ የቤኒንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ እጩ ከፍተኛ ድምጽ ማግኘታቸውን ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል።


በጋምቤላ ክልል ለክልል ምክር ቤት በዲማ ምርጫ ክልል በተሰጠ ድምፅ ደግሞ የብልፅግና ፓርቲ እጩዎች ትልቁን ድምፅ አግኝተዋል።


ምርጫ ቦርድ በትናትናው እለት በወታደራዊ እና በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካምፖች ውስጥ ስለተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ሂደትም ማብራሪያ ሰጥቷል።


በዚህም በ442 የወታደር ካምፖች የመከላክያ ሰራዊት አባላት፣ በ82 መጠለያ ጣቢያዎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ትናንት 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ድምጽ መስጠታቸውን ተናግሯል።


ቦርዱ ግንቦት 24 ምርጫ በተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች ከሁለቱ በስተቀር በሁሉም ምርጫ ክልሎች ውጤት ተለጥፏል ብሏል።


የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ሃይሉ ትናንት ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ በስካይ ላይት ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በ442 የወታደር ካምፖች 126498 ወታደሮች ደምጽ ለመስጠት ተመዝግበዋል ብለዋል።


በ82 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ደግሞ 28,632 ተፈናቃዮች ድምጽ ለመስጠት ተመዝግበዋል ብሏል ቦርድ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ።


ቦርዱ ከተመዘገቡ ከ28 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ መራጮች እና ከ126 ሺህ በላይ የመከላከያ ሰራዊት መራጮች ውስጥ ምን ያህሉ ድምጽ ሰጥተዋል የሚለውን ግን አልዘረዘረም።



መግለጫው እስከተሰጠበት ትናንት ምሽት 1:15 ድረስ በአንድ መከላከያ ካምፕ ደምጽ መስጠቱ እንዳልተጠናቀቀ የተናገሩት ሰብሳቢዋ በሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ካምፖች ግን 12 ሰዓት ላይ ድምጽ የመስጠት ሂደቱ ተጠናቅቋል ብለዋል።


ሰብሳቢዋ አይይዘው በመግለጫቸው ከሁለት ምርጫ ክልሎች በስተቀር የምርጫ ክልል ውጤት ተልጥፏል ሲሉ አስረድተዋል።


ውጤት ያልተለጠፈባቸው የምርጫ ክልሎች ሃላባ አንድ እና ቀብሪ በያ ምርጫ ክልሎች ናቸው ተብሏል።


ሀላባ አንድ ምርጫ ክልል ውጤት ድምር ተጠናቅቆ ያልተለጠፈበት ምክንያት የማዳመሩ ስራ ወደ ሆሳዕና ሄዶ እንዲሰራ የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች በመጠየቃቸው እንደሆነ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ሃይሉ ተናግረዋል።


የቅብሪ በያ ምርጫ ክልል ደግሞ ከጉርሱም፣ ከባቢሌ እና ከተለያዩ ወረዳዎች የተሰብስቡ ድምጾችን ለመደመር ጊዜ ስላስፈለገ ነው ብለዋል ሰብሳቢዋ።


ቦርዱ አሁን ላይ ከ1,139 ምርጫ ክልሎች፤ የ816 ምርጫ ክልሎችን ውጤት ወደ ማዕከል መግባቱን ተናግሯል።


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…









Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page