ሚያዝያ 9፣2016 - የአማራ ክልል መንግስት ሕወሃት በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ አሳሰበ
- sheger1021fm
- Apr 17, 2024
- 2 min read
የአማራ ክልላዊ መንግስት ሕወሃት በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ አሳሰበ፡፡
የክልሉ ሕዝብም ሕወሃት የከፈተውን ጥቃት እንዲመክት ጥሪ አስተላልፏል፡፡
የአማራ ክልላዊ መንግስት ይህን መግለጫ ያወጣው ሕወሃት የማንነት ጥያቄ ያለባቸውን የራያ አላማጣ፣ የራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ የኮረም እና ዛታ አካባቢዎች ላይ ወረራ ፈፅሟል ብሎ ነው፡፡
የሕወሃት የወረራ ድርጊት፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የጣሰ፣ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ እና ከፌዴራል መንግስቱ የተደረገውን የሰላም አማራጭ ውይይት የገፋ ነው ብሎታል፡፡
ሕወሖትና ለአራተኛ ጊዜ የጀመረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ከማድረግ እንዲታቀብና የፕሪቶሪያውን ስምምነት አክብሮ፣ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ የአማራ ክልል መንግስት ጠይቋል፡፡፡
ያ ካልሆነ፣ የክልሉ መንግስትና ሕዝቡ ከሌሎች ኢትዮጵያዊን ጋር ሆነው፣ አገርን ከመፍረስ ሕዝብንም ከጥቃት ለመከላከል እንደሚገደድ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡
በየደረጃው ያሉ የክልሉ የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅር አባላትም እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ ሕዝቡን በቁርጠኝነት እንዲያደራጁና እንዲጠብቁ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
የክልሉ ሕዝቡም ከየአካባቢው ከሚገኙት የአስተዳደር መዋቅሮች ጋር የጠበቀ ቁርኝነት እንዲፈጠርና እንዳለፈ ጊዜ ሁሉ የተከፈተውን ጥቃት እንዲመክት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የፌዴራሉ መንግስትም ሕወሃት ከወረራቸው አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ በማድረግ፤ ሕዝቡን ከጥፋት እንዲታደግ እና የሀገርን ሉአላዊነት ማስከበር እንደሚገባው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የአለም አቀፉማህበረሰብ እንደበፊቱ የተሳሳተ አቋም ሳይዝ የአፍሪካ ህብረትና አለም አቀፍ ታዛቢዎች በተገኙበት ሕወሃት ወረራ ማካሄዱን ተገንዝቦ በጥብቅ እንዲያወግዝ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ባለፉት ሳምንታት በራያና አላማጣ አካባቢዎች ግጭት መቀስቀሱን አስመልክቶ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት ጌታቸው ረዳ በኤክስ ማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፤ በሌሎች በሀይል በተያዙ በሚሏቸው የትግራይ ግዛቶች አካባቢዎች የደረሰውን ግጭት የፈጠሩት፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጠላት የሆኑ ሀይሎች ናቸው ብለው ነበር፡፡
ግጭቱ የደረሰውም ሁለቱ ወገኖች ችግሮቻቸውን ለመፍታት በአዲስ አበባ እየመከሩ በነበሩበት ወቅት መሆኑ አቶ ጌታቸው ጠቁመው ይሁንና ግጭቱን የፈጠሩት የሰላም ስምምነቱን ለማደፍረስ የፈለጉ ናቸው ከማለት አልፎ እነማን እንደሆኑ አልጠቀሱም፡፡

ከሳማንታት በፊት በአማራና በትግራይ ክልል መካከል የተጀመረውን ውዝግብን በተመለከተ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ፣ ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በኩል በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታየው አዝማሚያ ተገቢነት የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ ነው ብለው ነበር፡፡
የሚነሱ ጥያቄዎችም እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ወሰንን በሀይል እናስከብራለን የሚል አካሄድ፣ ካለፈው ስህተት አለመማርን ያመለካታል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: @ShegerFMRadio102_1
Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comentários