top of page

ሚያዝያ 6 2017 - 160.9 ቢሊዮን ብር ከገቢ ግብር መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ተናገረ።

  • sheger1021fm
  • Apr 14
  • 1 min read

160.9 ቢሊዮን ብር ከገቢ ግብር መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ተናገረ።


የከተማዋ ገቢ ሰብሳቢ ቢሮ የመገናኛ ብዙሃንን ጠርቶ  በሰጠው ማብራሪይ ባለፉት 9 ወራት ሰራሁት ያለውን ዘርዝሯል።


በተጠቀሰው ጊዜ ከገቢ ግብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረው 163.9 ቢሊዮን ብር ነበር።


ከዚህ ውስጥ የተሰበሰበው 160.9 ቢሊዮን ብሩ ነው ያሉት ማብራሪያውን የሰጡት የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ናቸው።

ቢሮው ባለንበት የ2017 የበጀት 230.4 ቢሊዮን ብር ከከተማዋ ለመሰብሰብ ውጥን ይዞ ወደ ስራ እንደገባ የተናገሩት አቶ ሰውነት፤ ተጨማሪ ገቢን ለመሰብሰብ የሚያስችሉ 14 የገቢ ርዕሶች መጨመራቸውንና ገቢ እየተሰበሰበባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።


ይህንን ስናደርግ ተጨማሪ የታክስ አይነቶችን እየጨመርን ሳይሆን ከዚህ ቀደም ታክስ መክፈል ሲገባቸው የማይከፍሉ እንዲሁም አሳንሰው ሲከፍሉ የነበሩ ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን እንዲከፍሉ በማድረግ ነው  ብለዋል።


ለአብነትም በዚህ ዓመት ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ ሲኖርባቸው ያልተመዘገቡ በሞሎች ውስጥ የሚነግዱ ነጋዴዎችን፣ ልኳንዳ ቤቶችንና ሬስቶራንቶችን ወደ ቫት በማስገባት የቫት ገቢን ከ812 ሚሊዮን ብር ወደ 1.7ቢሊዮን ብር ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።


በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የደሞዝ ግብር ይከፍሉኝ የነበሩት ግብር ከፋዮች ከ20 ሺህ ያልበለጡ ነበሩ የሚለው ቢሮው  በዘርፉ ያለውን ችግር በጥናት ከለየሁ በኋላ በተከተልኩት አሰራር የደሞዝ ግብር ከፋዮች ቁጥር 49 ሺህ ደርሷል ብሏል።


በሌላ በኩል ለቢሮው መክፈል የተገባቸውን ግብር ላለመክፈል የሚጠፉ፤ በተለያየ መንገድ ግብርን ሲሰውሩ የነበሩ ግብር ከፋዮችን ከፋይናንስ ኢንተለጀንስ አስተዳደር ጋር በመሆን እያደነ በማስከፈል ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም ተናግሯል።


ስራቸውን በመጠቀም ከግብር ከፋዩ እጅ መንሻ መቀበልን ጨምሮ ወደ ሌብነት የገቡ 12 የገቢዎች ቢሮ አመራሮችና 121 የቢሮው ሰራተኞች ተጠያቂ ተደርገዋል ተብሏል።


ይሁንና ማብራሪያውን የሰጡት የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ በአጥፊዎቹ ላይ ምን አይነት እርምጃ እንደተወሰደ ከመግለፅ ተቆጥበዋል።


ምንታምር ፀጋ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1


📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page