ሚያዝያ 6 2017 - በኢትዮጵያ የቤት ለቤት ህክምና አገልግሎት ቢዝነስ ምን መሳይ ይሆን?
- sheger1021fm
- Apr 14
- 1 min read
በኢትዮጵያ የቤት ለቤት ህክምና አገልግሎት ቢዝነስ ምን መሳይ ይሆን?
በኢትዮጵያ የቤት ለቤት ህክምና አገልግሎት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተፈላጊ እየሆነ ቢመጣም በመንግስት ተገቢው ቁጥጥር ስለማይደረግበት በዘፈቀደ የሚገባበት የስራ መስክ ሆኗል ሲል፤ በዘርፉ ከተሰማሩ ተቋማት መካከል የሆነው #ምርኩዝ የቤት ለቤት የጤና አገልግሎት የተባለው ድርጅት ተናገረ፡፡
ድርጅቱ ከ4 ዓመት በፊት ሲመሰረት በህክምና ተቋማት ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ቀሪ ህክምናቸውን በቤት ውስጥ እንዲያደርጉ የሚታዘዙ ህሙማንን መንከባከብን ታሳቢ አድርጎ እንደተመሰረተ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኛቸው ታምራት ነግረውናል፡፡

የቤት ለቤት የህክምና አገልግሎት፤እንደ አንድ አገልግሎት የሚሰጥ የቢዝነስ ዘርፍ የህግ ምዕቀፍ ወጥቶለት የሚሰራበት ነው ወይ? እናንተስ ህጋዊ ፈቃድ አላችሁ ወይ? ያልናቸው አቶ ዳኛቸው ሲመልሱ በምግብና መድሃኒት ባለስልጣን በሚሰጥ ፍቃድ የሚሰራ ስራ ነው፤ ይሁንና አብዛኞቹ ይህንን ስራ እንደ ቢዝነስ የሚሰሩት ምንም ዓይነት ፍቃድ ሳያወጡና የሚጠበቅባቸውን ግብር ሳይከፍሉ ነው፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ቤት ተከራይተን፣ ባለሙያ ቀጥረንና ግብር ከፍለን የምንሰራ በመሆኑ ተጎጂ ያደርገናል፤ ዘርፉ ቁጥጥር ይደረግበት ስንል ከጤና ቢሮ ጀምሮ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ብናመለክትም ሰሚ አጥተናል ብለውናል፡፡
ምርኩዝ የቤት ለቤት ህክምና አገልግሎት ለ24 ሰዓት ሙሉ የጤና እንክብካቤን ጨምሮ ከ1800-2ሺህ ብር ያስከፍላል ብለውናል ስራ አስኪያጁ፡፡
ለአጭር ጊዜ እንክብካቤ ለሚጠሩን የምንጠይቀው ከዚህም ያነሰ ዋጋ ነውም ብለውናል፡፡
የጤና ባለሙያውም ደህንነቱ ተጠብቆ ስራውን መስራት እንዲችል ታካሚውም የጠየቀውን አገልግሎት ማግኘት እንደሚችል መተማመኛ የሚሆን የውል ስምምነት ከታካሚው ጋር እንደሚፈራረሙ ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ ምርኩዝ የቤት ለቤት የጤና አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ከ20 በላይ በሆኑ ቋሚና ጊዜያዊ የህክምና ባለሙያዎች በቀን እስከ 10 ሰዎችን መድረስ እንደቻለ ከሃላፊው ሰምተናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
📌Spotify : https://shorturl.at/QG8f2
Comentarios