የብድር አቅርቦት እጥረት ለንግዱ ማህበረሰብ ስራ ማነቆዎች ተብለው ከተለዩ ችግሮች 40 በመቶውን ድርሻ ይይዛል ተባለ።
ለንግዱ ማህበረሰብ በሚቀርብ ብድርና ችግሮቹ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት ትናንት ተካሂዷል።
የዘርፉ የብድር አቅርቦት በርካታ ችግሮች የሚታዩበት እንደሆነ የውይይቱ አዘጋጅ የሆነው፤ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሠንበት ሸንቁጤ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው አባባል በቂ ብድር ለንግዱ ማህበረሰብ የማይቀርብ ሲሆን፤ ለብድር የሚጠየቀው ማስያዣ አይመጣጠንም።
ለብድር መመለሻ የሚሰጠው ጊዜም አነስተኛ እንደሆነ ወይዘሮ መሠንበት ተናግረዋል።
በምክር ቤታቸው ጥናት መሰረት የብድር አቅርቦት እጥረት፤ የንግዱ ማህበረሰብ ማነቆዎች ተብለው ከተለዩት 40 በመቶውን ድርሻ ይይዛል መባሉንም ጠቅስዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተወሰኑ ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት ለንግድ ኩባንያዎች ዋነኞች ብድር አቅራቢዎች ሆነው መቀጠላቸውን ያነሱት ወይዘሮ መሠንበት፤ የሚሰጡት ብድር ግን አነስተኛ እና ቅድመ ሁኔታዎች የበዙበት እንደሆነ አክለዋል።
ባንኮች በአመታዊ የብድር ድልድላቸው ለግሉ ዘርፍ የተወሰነ ኮታ ቢመድቡ፣ የብድር መያዣ ቅድመ ሁኔታዎችን በተወሰነ መልኩ ቢያላሉ እንዲሁም አንዳንድ ዘርፎች ከብድር መያዣ ነጻ የሚሆኑበትን መንገድ ቢጤን የሚሉ ምክረ ሀሳቦች በውይይቱ ላይ ሲሰጡ ሠምተናል።
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: @ShegerFMRadio102_1
Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments