ሚያዝያ 3 2017 - የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ያወጣውን መግለጫ እንደማይቀበለው ተናግሯል፡፡
- sheger1021fm
- Apr 11
- 1 min read
የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጋዜጠኞችን የመመዝገብና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መታወቂያ እሰጣለሁ ማለቱን ተከትሎ ከትናንት በስቲያ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ባወጣው መግለጫ ስራው የህግ መሰረት የለውም በሚል እውቅና እንደማይሰጠው ተናግሯል፡፡
ተቆጣጣሪ አካል የሆነው ባለስልጣኑ በመግለጫው ምክር ቤቱ ጋዜጠኞችን የመመዝገብም ሆነ የሙያ ማረጋገጫ የመስጠት ሃላፊነት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ አልተሰጠውም ብሏል፡፡
ምክር ቤቱ በበኩሉ አዋጁ ይፈቅድልኛል ባይ ነው፤የምክር ቤቱ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ታምራት ሃይሉ በአዋጁ በሚዲያዎችና በጋዜጠኞች መካከል በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ፤ሙያውን ሊያበረታ የሚችል የእርስ በእርስ ቁጥጥር ስርዓት እንዲኖር እውቅና የሰጠ በመሆኑ ስራውን የጀመርነው፤ የሙያ ማረጋገጫው የሚሰጠው ለሆኑ ፍቃደኛ ለሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አባል ለሆኑ ጋዜጠኞች በመሆኑ ከህግ ውጪ አያደርገንም ብለውናል፡፡

በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ የሙያ ስነ ምግባርና የመልካም አሰራር ደምብ ማውጣት ይቻላል የሚል የተቀመጠ በመሆኑ፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ለሙያተኛው ስልጠና ከሰጠን በኋላ የሙያ ብቃት ማረጋገጫውን ለመስጠት እንዳሰቡም በቶ ታምራት ያስረዳሉ፡፡
ባለስልጣኑ ይሁንታውን የማይሰጥ ከሆነ የተጀመረውን ስራ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል ላልናቸው የባለልንጣኑን ይሁንታ ባናገኝም ስለ ጉዳዩ እያስረዳን ስራችንን እንቀጥላለን ብለውናል፡፡
ስለ ጉዳዩ ለመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣኑ ስለ ጉዳዩ ቀድመን አሳውቀን ነበር፤ በጋራ የምንሰራቸው ስራዎች አሉ፤በሚቀጥለው ሳምንት ስለ ጉዳዩ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘናል ብለዋል፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንን ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ የጠየቅን ቢሆንም ባለስልጣኑ በመግለጫው ከጠቀሰው ውጪ ማብራሪያ እንደማይሰጥ ነግሮናል።
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
📌Spotify : https://shorturl.at/QG8f2
Comments