top of page

ሚያዝያ 29 2017 - ታሪክን የኋሊት ናዚዎች ዓለምን የማስገበር እና በስራቸው አዳሪ የማድረግ ምኞታቸው የወደቀበት ቀን

  • sheger1021fm
  • May 7
  • 1 min read

የጀርመን ናዚዎች ዓለምን የማስገበር እና በስራቸው አዳሪ የማድረግ ምኞታቸው ፀሀይ እንዳገኘው ጤዛ ተንኖ ሰራዊታቸው በተሸናፊነት እጅ የሰጠው የዛሬ 80 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ነው፡፡


የጀርመን ናዚዎች በአውሮፓ የ2ኛው የዓለም ጦርነት ከማብቃቱ ከ6 ዓመታት ገደማ በፊት ፖላንድ በመውረር የጥፋት ተልዕኳቸውን አሟሹ፡፡

ከዚህ አስቀድሞም የቀድሞዋን ቼኮቭሎቫኪያ ሱዴትን ግዛት ወደራሳቸው አድርገዋል፡፡

ናዚዎቹ በዚህ ብቻ አልጠረቁም፡፡


ቀስ በቀስ ብዙዎቹን የአውሮፓ አገሮች የወረራቸው ሰለባ አደረጓቸው፡፡

ፈረንሳይም ከናዚዎቹ የጥፋት ዘመቻ አላመለጠችም፡፡


የናዚዎቹ ወረራ እስከ ሩሲያዋ ርዕሰ ከተማ ሞስኮ በራፍም የተቃረበ ነበር፡፡


ናዚዎቹ ለጥፋት ዘመቻቸው ከጣሊያን ፋሽስቶች እና ከጃፓን ተስፋፊዎች ተሻረኩ፡፡


ይሄ የጥፋት ቁርኝት የአክሲስ ሀይል ተባለ፡፡


በአንፃሩ አሜሪካ ፣ ብሪታንያ ፣ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት የህብረቱ እና የጦር ተባባሪዎቻቸው ሀይሎች ተብለው እነ ናዚ ጀርመንን ለመመከት ተቆራኙ፡፡

በጦርነቱ አጋማሽ የውጊያው ገፅታ መለወጥ ያዘ፡፡


የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት ጦር የናዚዎቹን ሀይል በስታሊንግራድ ማንኮታኮቱ የናዚዎቹ ጀምበር እየጠለቀች ለመምጣቷ ቀዳሚው ምልክት ሆነ፡፡


የህብረቱ ሀይሎች በሰሜናዊ ፈረንሳይ ኖርማንዲ በአየር እና ባህር ወለድ ዘመቻ የናዚን አከርካሬ መምታታቸው የመጨረሻው መጀመሪያ ሆነ፡፡

ከዚህ በኋላ ናዚዎቹ አቅምም ፣ ጊዜም ፣ ወኔም እየከበዳቸው መጣ፡፡

በሽንፈት ላይ ሽንፈት ተደራረበባቸው፡፡


የህብረቱ ሀይሎች ከየአቅጣጫው ያሳድዷቸው ያዙ፡፡

የናዚ ሰራዊት ወደ አገሩ ቢሸሽም አገሩ መሸሻ ልትሆነው አልቻለችም፡፡

ከየአቅጣጫው የህብረቱ ሀይሎች ከበቡት፡፡


የእነ አሜሪካ እና ብሪታንያ ሀይሎች ከምዕራብ ፣ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ሰራዊት ደግሞ ከምስራቅ አቅጣጫ መፈናፈኛ አሳጡት፡፡


የጀርመን ከፍተኛው ወታደራዊ እዝ የዛሬ 80 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እጅ ለመስጠት ተገደደ፡፡


በእጅ መስጫው ሰነድ ላይም በፈረንሳይ ሪምዝ የናዚዎቹ ጦር የዘመቻ መመሪያ የበላይ ጄኔራል አልፍሬድ ዮደ ፊርማውን አኖረበት፡፡


ሆኖም የቀድሞ ሶቪየት ህብረት ለቀዳሚው እጅ መስጫ ሰነድ እውቅና መስጠት ባለመፍቀዷ በማግስቱ የጀርመን መንግስት መቀመጫ በነበረችው በርሊን በህብረቱ ሀይሎች የጦር አዛዦች እና በጀርመናዊው ፊልድ ማርሻል ዊል ሔልም ካይትል መካከል የናዚዎች 2ኛ እጅ መስጫ ሰነድ መፈረሙ በታሪክ ሰፍሮ ይገኛል፡፡


በዚህም በአውሮፓ የ2ኛው የዓለም ጦርነት መደምደሚያ ሆነ፡፡


Comentários


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page