top of page

ሚያዝያ 28፣2016 - በሀላባ ዞን የተከሰተው ጎርፍ የቁሊቶ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና መሳሪያዎችን አውድሟል ተባለ

በሀላባ ዞን የተከሰተው ድንገተኛ ጎርፍ በዞኑ ዋና ከተማ የሚገኘውን የቁሊቶ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና መሳሪያዎችን አውድሟል ተባለ፡፡


በዚህም የተነሳ የሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት ተስተጓጉሏል ተብሏል፡፡


በሀላባ ዞን ሚያዝያ 26/2016 ዓ.ም ድንገት በተከሰተ ጎርፍ የ5 ሰዎች ህይወት ማለፉ መነገሩ ይታወሳል፡፡


ከእነዚህ በጎርፍ ከተወሰዱ ሰዎች መካከል፤ የሶስት ሰዎች አስክሬን እንደተገኘና የሁለቱን ሰዎች አስክሬን በማፈላለግ ላይ እንዳለም ዞኑ ተናግሯል፡፡

በጎርፍ ሕይወታቸው ካጡት መካከል፤ 3ቱ ከ7 እስከ 12 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊ ልጆች ሲሆኑ ከብቶችን እንየጠበቁ ባሉበት ወቅት ነው በጎርፍ የተወሰዱት ተብሏል፡፡

ይህንን ለሸገር የተናገሩት የሀላባ ዞን መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ሐሩና አሕመድ ናቸው፡፡


የተከሰተው ጎርፍ ከሰው ሕይወት መቅጠፍ በተጨማሪም በዞኑ ዋና ከተማ የሚገኘውን የቁሊቶ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና መሳሪያዎችን አውድሟል ብለዋል ሀላፊው፡፡


በዚህ የተነሳም ለበርካታ ታካሚዎች አገልግሎት የሚሰጠውን የቁሊቶ አጠቃላይ ሆስፒታል አገልግሎት ተስተጓጉሏል ሲሉ አቶ ሐሩና ተናግረዋል፡፡


ወደ ሆስፒታሉ የገባው ከፍተኛ መጠን ያለው ጎርፍም እንዲወጣ እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡


በሆስፒታሉ ላይ የደረሰው አጠቃላይ ውድመት የገንዘብ ስሌት አሁን እንዳልታወቀም አንስተዋል፡፡


ጎርፉ በድንገት የተከሰተው እና ጉዳት ያደረሰው በዞኑ በሚገኙት፤ ወይራ ድጁ እና አቶቴ ውሉ በተባሉ ወረዳዎች እንደሆነም ተነግሯል፡፡


በጎርፍ አደጋው በ30 ሄክታር ላይ የለማው የበቆሎና የቦለቄ ሰብል ወድሟል ተብሏል፡፡

14 ፍየሎች መሞታቸውንም ተናግረዋል፡፡


ጎርፉ ወደ ሻላ ሀይቅ የሚገባ በመሆኑ ያልተገኙ አስክሬኖች ምናልባትም ወደሀይቁ የሚገቡበት እድል ሰፊ በመሆኑ በሀይቁ ላይ ፍለጋው እየተደረገ መሆኑን አቶ ሀሩና ተናግረዋል።

ጊዜው የዝናብ ወቅት በመሆኑ ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል።


ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየጣለ ባለው ዝናብ የሚከሰት ጎርፍ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡


በሀገር አቀፍ ደረጃ በመጪዎቹ ቀናትም ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ማሳሰቡ አይዘነጋም፡፡


ማንያዘዋል ጌታሁን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

Comments


bottom of page