top of page

ሚያዝያ 24፣2016 - የእስራኤል ፍልስጤም ጦርነት ወደ ውጪ በሚላክ የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ ተጽዕኖውን እያሳረፈ ነው ተባለ

የእስራኤል ፍልስጤም ጦርነት ወደ ውጪ በሚላክ የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ ተጽዕኖውን እያሳረፈ ነው ተባለ።


ጦርነቱ ምርቶቹን ለሚያጓጉዙ የመርከብ ኩባንያዎች የሚፈጸመውን ክፍያ በትንሹ ከሁለት ሺህ ዶላር በላይ እንዲጨምር ማድረጉ ተነግሯል።


የምርቶቹ የማስረከቢያ ጊዜ እንዲራዘም እያስገደደ ነውም ብሏል የኢትዮጵያ አትክልት፤ ፍራፍሬ ፤ ስራ ስር እና መዓዛማ ውጤቶች አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር።


ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው ምርቶች መካከል አበባ ፤ አትክልት፤ ፍራፍሬ ፤ ስራ ስር እና መዓዛማ የሆኑ ውጤቶች ይገኙበታል።


ይህ ዘርፍ ከቡና ቀጥሎ ለኢትዮጵያ ዶላር በማምጣት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው።


በ2016 በጀት አመት ስምንት ወራት ያለውን አፈጻጸም እንኳን ስናይ ከ310 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በማስገኘት በዚሁ ደረጃው ላይ ተቀምጧል።


በስምንት ወራቱ ቡና ከ715 ሚሊየን ዶላር በላይ በማስገባት ቀዳሚው ነው።

ከተቀሰቀሰ ወራትን ያስቆጠረው የእስራኤል ፍልስጤም ጦርነት ግን በተለይ፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ፤ ስራ ስር እና መዓዛማ የሆኑ ውጤቶችን ንግድ እየፈተነው ነው ተብሏል።


ምርቶቹን የሚያጓጉዙ የመርከብ ኩባንያዎች ቀይ ባህርን በመተው በደቡብ አፍሪካ በኩል ዞረው እንዲሄዱ ነው ሲሉ ፤የኢትዮጵያ አትክልት፤ ፍራፍሬ ፤ ስራ ስር እና መዓዛማ ውጤቶች አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ ተናግረዋል።

በችግሩ ምክንያት የምርት ማጓጓዣ ኮንቴነሮች እጥረት አጋጥሟል የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ ፤ የመርከቦች የቆይታ ጊዜ መራዘሙን እና የማጓጓዣ ክፍያውም በትንሹ ከሁለት ሺህ ዶላር በላይ መጨመሩን አክለዋል።

የአበባ ምርት ግን አሁንም ድረስ ወደ ገዥ አገራት የሚላከው በአውሮፕላን ነው፡፡


ከአበባ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ስራ ስር እና መዓዛማ ምርቶች አበባ አሁንም ከፍ ያለውን ገቢ በማምጣት ቀዳሚው መሆኑ ተነግሯል።


አትክልት ብቻውን ተለይቶ ሲታይ ደግሞ ድርሻው ከ15 በመቶ በታች እንደሆነ ከዋና ዳይሬክተሩ ሠምተናል።


ኢትዮጵያ ግን ለአትክልት ልማት የተመቸ ተፈጥሮ እና ምቹ ዕድል አላት ብለዋል።


ለልማቱ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ማሟላት እና ተቀናጅቶ መስራት ኢትዮጵያ ከአትክልት የምታገኘውን ገቢ ያሳድጋሉ ከተባሉ የመፍትሄ ሃሳቦች መካከል ናቸው፡፡


ኔዘርላንድስ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን እና ጣሊያን የኢትዮጵያን የአበባ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ ፣ ስራ ስር እና መዓዛማ ምርቶች ከሚገዙ ሀገራት መካከል ናቸው፡፡


አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ኮሪያ እና አውስትራሊያም ሌሎቹ እንደሆኑ ሠምተናል።


ንጋቱ ረጋሣ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

Comments


bottom of page