top of page

ሚያዝያ 22 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Apr 30
  • 1 min read

ወደብ አልባዎቹ ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል መውጫ ሊያገኙ ነው፡፡


የሞሮኮ መንግስት ሶስቱ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች በግዛቱ በኩል ወደ አትላቲክ ውቅያኖስ መውጫ እንዲያገኙ ሀሳብ ማቅረቡን አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡


የ3ቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከሞሮኮ ንጉስ ሞሐመድ 6ኛ ጋር በራባት ባደረጉት ምክክር በሀሳቡ ተስማምተንበታል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ከምዕራብ አፍሪካ መንግስታት ምጣኔ ሐብታዊ ማህበር /ኤኮዋስ/ አባልነታቸው ለቅቀው ወጥተዋል፡፡


በአንፃሩ የራሳቸውን የሳሕል መንግስታት ትብብር የተሰኘ ኮንፌዴራላዊ ጥምረት መፍጠራቸው ተጠቅሷል፡፡


ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ በግልበጣ ስልጣን በጨበጡ ወታደራዊ መንግስታት እየተዳደሩ ነው፡፡



የዩክሬይን የቀድሞ ፕሬዘዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች በህገ-ወጥ መንገድ የአገሪቱን ድንበር በማለፍ በሌሉበት የ15 አመታት የእስር ቅጣት ተፈረደባቸው፡፡


ያኑኮቪች ህዝባዊ እምቢታ በበረታባቸው ወቅት ድንበር አቋርጠው ወደ ሩሲያ የገቡት ከ11 አመታት በፊት እንደነበር አናዶሉ ፅፏል፡፡


ቪክቶር ያኑኮቪች በወቅቱ ተገቢውን የድንበር ቁጥጥር ማጣሪያ ሳያሟሉ ሩሲያ የገቡት በአውሮፕላን ተጓጉዘው እንደነበር በመረጃው ተጠቅሷል፡፡


በጊዜውም የዩክሬይን የደህንነት መስሪያ ቤት የበላይ የነበሩ ግለሰብም በዚሁ ጉዳይ የ10 አመታት እስር እንደተፈረደባቸው ታውቋል፡፡


ያኑኮቪች ከዚህ ቀደምም በአገር ክህደት የ13 አመታት እስር ተፈርዶባቸው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡


ዩክሬይናውያን ቪክቶር ያኒኮቪች ከስልጣን የተባረሩባትን ሂደት አብዮት ሲሉ ይጠሩታል፡፡



በናይጀርያ ቦርኖ ግዛት በጎዳና ላይ በተጠመደ ፈንጂ በጥቂቱ 26 ሰዎች ተገደሉ፡፡


የቦርኖ ግዛት የፅንፈኛ ታጣቂዎች ተፅዕኖ ያየለበት እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡


ተቀባሪ ፈንጂው ጉዳት ያደረሰው ናይጀሪያ ከካሜሩን ጋር በምትዋሰንበት አቅራቢያ ነው ተብሏል፡፡


የናይጀሪያ የፀጥታ ሀይሎች ከIS የምዕራብ አፍሪካ ቅርንጫፍ እና ከቦኮ ሐራም ፅንፈኛ ቡድኖች ጋር ሲተናነቁ በርካታ አመታትን አስቆጥረዋል፡፡


ያም ሆኖ ፅንፈኞቹ አሁንም ድረስ ጥቃት ከመፈፀም እና የፀጥታ ስጋት ከመፍጠር አለመቆጠባቸው ይነገራል፡፡


ፅንፈኞቹ ከናይጀሪያ በተጨማሪ የጥፋት አድማሳቸውን ወደ አጎራባች አገሮችም ማስፋታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comentarios


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page