top of page

ሚያዝያ 22 2017 -በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ ኑሮን ለማሸነፍ ስላላስቻላቸው ማታ ማታ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ መኖራቸውን በጥናት መለየቱን የጨርቃ ጨርቅ ፌዴሬሽን ተናግሯል

  • sheger1021fm
  • Apr 30
  • 2 min read

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ ኑሮን ለማሸነፍ ስላላስቻላቸው ማታ ማታ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ መኖራቸውን በጥናት መለየቱን የጨርቃ ጨርቅ ፌዴሬሽን ተናግሯል፡፡


በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ ለኑሮ ስለማይበቃቸው ማታ ማታ ከሆቴሎች ትርፍራፊ ምግቦችን ይዘው ወደ ቤታቸው የሚገቡ እንዳሉም ፌደሬሽኑ ጠቁሟል፡፡


አምራች ስራተኛ፣ ምቹ ስራ ለወጣቶች እና ሴቶች በጨርቃ ጨርቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ መፍጠር በሚል ርዕስ የፖሊሲ አቅጣጫ ተቋሚ ጥናት ለማድረግ የማህበራት ጥናት መድረክ (Forum For Social Studies) በጠራው የሁለተኛ ዙር የባለድርሻ አካላት ወይይት ላይ የተገኙት የጨርቃ ጨርቅ ፌዴሬሽን ተወካይ አቶ ተስፋዬ አብዲሳ ‘’የሚከፈላቸው ደመወዝ ለኑሮ ስለማይበቃቸው ማታ ማታ ከሆቴሎች ተመላሽ ምግቦችን ይዘው የሚገቡ እንዳሉም በጥናት አረጋግጠናል’’ ብለዋል፡፡


በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ስራተኞች ገቢ እንዲሻሻል ለማድረግ ዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ማፅደቅ አንዱ መፍትሄ ነው፤ ያሉት ተወካዩ ‘’በተለይ ሴቶች ክፍያው ዝቅተኛ ስለሆነ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ መኖራቸውን በጥናት አረጋግጠናል’’ ሲሉ አስረድተዋል፡፡


ፌዴሬሽኑ ባካሄደው ጥናት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ አሰሪዎች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን ፈቃደኞች እንዲሆኑ አረጋግጧል ተብሏል፡፡


መንግስት ግን እግሩን የሚጎትትበት ምክንያት ግልፅ እንዳልሆነ ሰምተናል፡፡


ሌላ የውይይት ተሳታፊ በበኩላቸው በኢንዲስትሪ ፓርኮች በጨርቃ ጨርቅ እና ጋርመንት ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች የሚከፈላቸው ክፍያ ዝቅተኛ በመሆኑ በትዳር ሕይወታቸው ላይ እንኳን የመወሰን መብት እንዳይኖራቸው አድርጓል ብለዋል፡፡


ትዳር የሚመሰርቱት ስለፈለጉ ሳይሆን ወጪ ለመጋራት በሚል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡


የኢትዮጵያ ስራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አማካሪ እንደሆኑ የነገሩን ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ዘሪሁን ገዛኸኝ በበኩላቸው ኮንፌዴሬሽኑ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን መጠየቅ ከጀመረ በርካታ ዓመታት ሆኖታል እስካሁን ግን መፍትሄ አላገኘም ብለዋል፡፡


አቶ ዘሪሁን የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሰራተኞች ወርሃዊ ክፍያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲተያይ እጅግ ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡


የጥናት ቡድኑ አባል የሆኑት ደግነት አበባው(ዶ/ር) በበኩላቸው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጉዳይ አስፈላጊነቱ እንዳማያጠራጥር ተናግረው ነገር ግን እንዴት ይወሰን የሚለውን በደንብ ማየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡


የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ነገ ሀሙስ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ136ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሰራተኞች ቀንን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ የዝቀተኛ ደመወዝ ወለል እንዲወስን የጠየቀው ጥያቄ መልስ እንዳላገኘለት ተናግሯል፡፡


የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ ተጠይቆ የዝቀተኛ ደመወዝ ወለል ጉዳይ ከዐቢይ ኢኮኖሚ ጋር የሚገናኝ ስለሆነ በጥንቃቄ ነው መታየት ያለበት የሚል ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…..




ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page