ሚያዝያ 22 2017 - ለ17 ዓመታት ኦዲት ሳይደረጉ የቆዩ በህብረት ስራ ማህበራት ስር የሚተዳደሩ 3,000 የገቢ ማስገኛ ተቋማት እንደተገኙ ተነገረ፡፡
- sheger1021fm
- Apr 30
- 1 min read
በአዲስ አበባ ለ17 ዓመታት ኦዲት ሳይደረጉ የቆዩ በህብረት ስራ ማህበራት ስር የሚተዳደሩ 3,000 የገቢ ማስገኛ ተቋማት እንደተገኙ ተነገረ፡፡
ከተቋማቱ በሚገኘው ገቢም አመራሮች ሲጠቀሙባቸው ነበሩ ተብሏል።
በህብረት ስራ ማህበራት ስር ያሉት እነዚህ ገቢ ማስገኛ ተቋማት ላለፉት 17 ዓመታት ኦዲት ሳይደረጉ እንደቆዩና፤ ከእነዚህ ተቋማት የሚገኘው ገቢ በሙሉ ለተቋማቱ ሳይሆን ተቋማቱን የሚመሩ #ግለሰቦች ተጠቃሚ እየሆኑባቸው ነበረ ተብሏል፡፡
የህብረት ስራ ማህበራቱ የተለያዩ ቤቶች እንዳላቸው የተነገረ ሲሆን እነዚህን ቤቶች ለራሳቸው እየተጠቀሙ ሳይሆን ለነጋዴዎች እያከራዩት እንደቆዩ ተነግሯል፡፡ ከእነዚህ ቤቶች የሚገኘው ገቢ ነው ተቋማቱ የሚመሩት ግለሰቦች እየተጠቀሙበት ቆይተዋል የተባለው፡፡

ይህ መሆኑ የታወቀው በቅርቡ በተቋሙ ተደረገ በተባለ ፍተሻ እና የማሻሻያ ስራ እንደሆነ ዛሬ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባደረገው ጉባኤ ላይ ሲነገር ሰምተናል፡፡
እየተደረገ ነው በተባለው የማሻሻያ ስራ፤ የህብረት ስራ ማህበራት ያላቸውን ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማድረግ በብርቱ እየተሰራ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
በእዚህም ለግል ነጋዴዎች ተከራይው ቆይተዋል ከተባሉት 3000 ቤቶች መካከል፤ 500ዎቹ እንዲለቁ መደረጉንና ከእነዚህም ውስጥ 120ቹ ብቻ እንደ አዲስ አዘጋጅቶ የህብረት ስራ ማህበራቱ ራሳቸው እንዲሰሩባቸው እየተደገ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የራሳቸው መለያ ሊደረግባቸው ሲገቡ የሚተዋወቁት እና የሚለዩት #የመጠጥ_ፋብሪካዎች በሚቀቧቸው ቀለሞች ነው ተብሏል፡፡ ይህ መሆኑም ልክ አይደለም፤ ሊታወቁ እና ሊለዩ የሚገባው በራሳቸው መለያ(ብራንድ) እንደሆነም ተነግሯል፡፡
የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን በስሩ 9,000 ማህበራት እንደሉ ተነግሯል፡፡ እነዚህን በሙሉ ኦዲት ለማድረግ የባለሞያ እጥረት አለበትም ተብሏል፡፡ ተቋሙ ያሉት የኦዲት ባለሞያዎች በቁጥር ድግሞ 147 ብቻ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡
በእነዚህ ውስን የባለሞያዎች ቁጥር፤ 9,000 ማህበራትን ኦዲት ማስደረግ ስለሚከብድ የቅድሚያ የሚሰጣቸው ማህበራትን በመለየት እየተሰራ እንደሆነም የተቋሙ ሀላፊዎች አስረድተዋል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comments