top of page

ሚያዝያ 22፣2016 - በኢትዮጵያ ከጠቅላላው ህዝብ 5 በመቶው ሲጋራ አጫሽ እንደሆኑ ጥናት አሳየ

ሀገሪቱ የሲጋራ አጫሾችን ቁጥር በመቀነስ ስኬታማ ሀገራት ከሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ናትም ተብሏል፡፡


ህጻናትን ከትንባሆ ነጻ የማደረግ እንቅስቃሴ(Campaign for Tobacco Free Kids) የተባለ ድርጅት ኢትዮጵያ ያለባትን የትንባሆ አምራቾች እና ተጠቃሚዎች ግፊትን ተቋቁማ ለውጥ አምጪ የትንባሆ ቁጥጥር አዋጆች ማጽደቋን አድንቋል፡፡


ድርጅቱ የትምባሆ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ የተደረጉ ጥረቶችን እና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ያጠናቀረውን ተራኪ እና ዘጋቢ ተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ አድርጓል፡፡

የዚህ ዓለም አቀፍ ጤና ተቋም የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬከተር ቢንቶው ካማራ የትንባሆ ቁጥጥሩ ውጤታማነት መሰረት ያደረገው የተለያዩ መንገስታዊ ተቋማት በሀብረት ከመስራታቸው ባለፈ እንደ ሀገር የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖሩ ነው ብለዋል፡፡


ይህ አዲስ ዘጋፊ ፊልም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለትንባሆ ቁጥጥር አዋጅ እና እንቅስቃሴ ያደረገችውን በርካታ ውጣ ውረዶች ያካተተ ሲሆን፤ በሂደቱም ላይ የነበሩትን ባለድርሻ አካላት በተለይም ደግሞ ድጋፍ እና ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ ተቋማት በዋናነት የዓለም የጤና ደርጅትን የትንባሆ ቁጥጥር የህግ ማዕቀፍን ተንተርሰው ድጋፍ ያደረጉ አካላትን ትኩረት አድርጓል።


ዘጋቢ ፊልሙ ጌትፊልድ በተባለ እና ማኅበረሰባዊ ለውጥ ለማምጣት በሚል የተቋቋመ ኩባንያ ባለቤትነት የተዘጋጀ ሲሆን፤ ዝግጅቱ ከፍተኛ ርብርብ የተደረገበት ሲሆን የኢትዮጵያ የማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ኃላፊዎች ጋር ቃለ ምልልስን ያካተተ እንደሆነ ተነግሯል፡፡


በኢትዮጵያ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከአጫሾች በሚወጣ የትምባሆ ጭስ እንደሚቸገሩ ከዚህ በፊት የተደረገ ጥናት አሳይቷል፡፡


እንደ ሀገር በኢትዮጵያ ከጠቅላላው ህዝብ ውስጥ 5 በመቶ ያህሉ ትምባሆ አጫሾች ሲሆኑ ሀገሪቱ የአጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ እና የዜጎችን ጤንነት ለመጠበቅ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ በየጊዜው ስታዘጋጅ ቆይታለች፡፡


ትምባሆ መግዛት የሚችሉት እድሜያቸው ከ21 ዓመት በላይ የሆኑ፣ የመዝናኛ እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ትምባሆ ማጨስ መከልከሉ፣ ሰው በተሰበሰበባቸው ቦታው ትምባሆ ማጨስ እና መስጨስ መከልከሉ ከተወሰዱ እና አስገዳጅ ከሆኑ እርምጃዎች መካከልም ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በተጨማሪም በትምባሆ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ግብር መጣሉ እና የትምባሆ ምርቶችን በብዙሃን መገናኛዎች ላይ ማስተዋወቅ እንዳይቻል መከልከሉም ኢትዮጵያ የትምባሆ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከመቀነስ አንጻር ከሰራቻቸው ስራዎች መካከል መሆናቸው ይታወሳል፡፡


ኢትዮጵያ ይህ ጥረቷ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አንጻር ከትምባሆ ነጻ የሆኑ ህጻናትን ለመፍጠር ብርቱ ጥረት እያደረጉ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን አድርጓታልም ተብሏል፡፡


ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





תגובות


bottom of page