ሚያዝያ 2 2017 - ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው መስራት የሚፈልጉ የውጪ ባንኮች 40 ሚሊየን ዶላር ካፒታል ማስመዝገብ አለባቸው ተብሏል
- sheger1021fm
- Apr 10
- 2 min read
ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው መስራት የሚፈልጉ የውጪ ባንኮች 40 ሚሊየን ዶላር ካፒታል ማስመዝገብ አለባቸው ተብሏል።
ገንዘቡ የሀገር ውስጥ ባንኮች ሲቋቋሙ ከሚጠየቁት አምስት ቢሊየን ብር ጋር የተቀራረበ ምንዛሪ አለው።
ለመሆኑ የተጠየቀው 40 ሚሊየን ዶላር ካፒታል የውጪ ትላልቅ ባንኮችን ምን ያህል ወደ ኢትዮጵያ ሊጋብዝ ይችላል?
የውጪ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ የሚፈቅድ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወሳል።
የአዋጁን መውጣት ተከትሎ ደግሞ የፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ በብሄራዊ ባንክ ይፋ ሆኗል።
መመሪያው የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ስራ ለመጀመር ከአምስት ቢሊየን ብር ጋር ተቀራራቢ የሆነ ምንዛሪ ያለው 40 ሚሊየን ዶላር ካፒታል ማስመዝገብ እንዳለባቸው ይጠቅሳል።

ስለ ገንዘቡ ምንጭ የሚገልጽ ማስረጃ ማቅረብ እንዳለባቸውም መመሪያው ይደነግጋል።
የውጪ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰሩ የተፈቀደው በአራት መንገዶች ሲሆን የመጀመሪያው ተቀጥላ ወይም ሰብሲደሪ ባንክ መክፈት ነው።
ቅርንጫፍ በመክፈትም መስራት ይችላሉ የተባለ ሲሆን የውክልና ቢሮ በኢትዮጵያ ኖሯችው መስራት እንደሚችሉም ተነግሯል።
አራተኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ባንኮች አክሲዮን ወይም ድርሻ የሚገዙበት ነው።
ባንኮቹ እንዲያስመዘግቡ የተጠየቁት ካፒታል በውጭ ምንዛሪ ቢሆንም ተመኑ የአገር ውስጦቹ ሲቋቋሙ ከሚጠየቁት አምስት ቢሊየን ብር ጋር የተቀራረበ ተመን ያለው ነው።
የተቀመጠው የካፒታል መጠን በርከት ያሉ እና አቅም ያላቸውን የውጪ ባንኮች ምን ያህል ወደ ኢትዮጵያ ሊጋብዝ ይችላል ይሆን?
ጥያቄውን ያቀረብንላቸው የምጣኔ ሃብት ባለሞያው አቶ ክቡር ገና አይመስለኝም ይላሉ።
የውጪ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው ሲሰሩ በዋናነት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ምን አይነት ስራ መስራት አለባቸው ? ፤
እንዲሁም የቁጥጥር ሥርዓቱ ምን ይምሰል? የሚለው ላይ ሊሆን ይገባል ሲሉም አቶ ክቡር ተናግረዋል።
የመመሪያው መውጣት የውጪ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው የሚሰሩበት ጊዜ መቃረቡን አመልካች ይመስላል።
ከዚህ አንጻር የአገር ውስጥ ባንኮች ተወዳዳሪ ሆነው ለመገኘት አሁን ላይ ምን ማድረግ ይኖርባቸው ይሆን?
በተለይም ተደጋግሞ በሚነሳው የውህደት ሃሳብ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን አቶ ክቡርን ጠይቀናቸዋል።
የወጣው መመሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት የሚፈልጉ የውጪ ባንኮች ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን በሰነድ ማሟላት እንዳለባቸውም ያዛዝል።
የአዋጭነት ጥናት ማቅረብ ፤ የባንኩን ባለቤቶች ዝርዝር ማሳወቅ እና፤ ባንኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ሚሰራው ስራ መዘርዘር በሰነዱ መሟላት አለባቸው ከተባሉ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
ንጋ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
📌Spotify : https://shorturl.at/QG8f2
Comments