ሚያዝያ 2 2017 - “መምህራን እየተራቡ የትምህርትን ጥራት ማረጋገጥ አይቻልም” መምህራን
- sheger1021fm
- Apr 10
- 1 min read
“መምህራን እየተራቡ የትምህርትን ጥራት ማረጋገጥ አይቻልም” መምህራን
“የመምህራንን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ትምህርትን ለማሻሻል በጣም ወሳኝ ነው” የትምህርት ሚኒስቴር
ትውልድ ፊደል ቆጥሮ ከህልሙ እንዲደርስ መንገድ ጠራጊው፣ አቅጣጫ ጠቋሚው መምህር ለሞያው የሚከፈለው ክፍያ ዝቅተኛ በመሆኑ ለማስተማር ፍላጎት እንዲጣ ምክንያት እንደሆነ ጥናት አሳይቷል፡፡
በደባርቅ ዩኒቭርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ፈለቀ ወርቁ “የዩኒቭርሲቲ መምህራን ሀገር እንድትቀጥል የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረው ይህን ማድረግ የሚችሉት ግን ሳይርባቸው ማስተማር ሲችሉ ነው” ብለዋል፡፡
“የዩኒቭርሲቲ መምህራን እየተራቡ ሀገርን አያስቡም ያሉት መምህሩ አሁን ለመምህራን እየተከፈለ ያለው ክፍያ ከአንድ የባንክ ቤት የጥበቃ ሰራተኛ ያነሰ ነው” ሲሉ ነግረውናል፡፡
በዚህም ምክንያት መምህሩ ሞያውን ለቆ ወደ ሌላ ስራ እየገባ ነው ያሉት አቶ ፈለቀ ወርቁ ‘’መምህሩ ኑሮ አይደለም እየኖረ ያለው ከኑሮ በታች ነው’’ ብለዋል፡፡
የመምህር ኑሮ በቃል የሚገለጽ አይደለም ከሚያስተምረው የሚማረው ተማሪ የተሻለ ለብሶ እየገባ፣ የተሸለ ኑሮ እየኖረ በሁሉ ነገር ዝቅ ያለ መምህር እንዴት ተማሪ ፊት ቆሞ ነው ማስተማር የሚችለው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‘’መምህሩ ዛሬ የተቀደደ ሱሪ ነው ልብሶ የሚሄደው ካለሲ መቀየርያ አጥቷል’’ ሲሉ መምህሩ ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፍተና ውጤት ማሽቆልቆልን ምክንያት ለማውቅ ያስጠናው ጥናት መምህራን የሚከፈላቸው ክፍያ ዝቅተኛ መሆኑ የማስተማር ፍላጎታቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የጠቆመ ነበር፡፡
ጥናቱ ለውይይት በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅትም በወይይቱ የተሳተፉ የትምህርት ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፣ መምህራን እና የምክርቤት አባላት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመምህሩን ኑሮ ማሻሻል ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በወቅቱ የተገኙት እና ማብራሪያ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የመምህራንን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ከፋይናንስ ሥርዓት ጋር ለማስተሳሰር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ይሁንና የመምህራን የደመወዝ ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ቢደርስም ለዓመታት እልባት ሳያገኝ የቀጠለ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…..
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
📌Spotify : https://shorturl.at/QG8f2
Comments