ሚያዝያ 16 2017 - የብራዚሉ አውሮፕላን አምራች ኢምብሬር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር አብሮ ለመስራት ንግግር መጀመሩን ተናገረ
- sheger1021fm
- Apr 24
- 1 min read
የብራዚሉ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ኢምብሬር (Embraer) ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተለያዩ መስኮች አብሮ ለመስራት ንግግር መጀመሩን ተናገረ፡፡
የኢምብሬር ሀላፊዎችም በአዲስ አበባ ይገኛሉ፣ ለጋዜጠኞችም መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኩባንያው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር አብሮ ለመስራት ስላሰበባቸው ጉዳዮች በዝርዝር ባያፍታታም ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የትብብር ፍላጎት እንዳለው ግን አስረድቷል፡፡

"የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን መግዛት ሲፈልግ የሚገዛውን አውሮፕላን መጠገን እንደሚችልና ጥገናውም እዚሁ አዲስ አበባ ማድረግን እንደሚያረጋግጥ እንረዳለን" ያሉት የኢምብሬር ሃላፊዎች አብሮ የመስራት ፍላጎቱም ይህንን ከግምት ያስገባ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
ንግግሩ ፍሬ የሚያፈሩና #የኢትዮጵያ_አየር_መንገድ የኢምብሬር ስሪት አውሮፕላኖችን የሚገዛ ከሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል፡፡
1962 ዓ.ም የተቋቋመው የብራዚሉ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ኢምብሬር በግዝፈቱ ከቦይንግና ከኤር ባስ ቀጥሎ በአለም ላይ በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
ኩባንያው እስካሁን ድረስ 9,000 አውሮፕላኖች ሰርቶ ለተለያየ አየር መንገዶች ማስረከቡንም ሀላፊዎቹ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡
ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው እንዲሁም ዝቅተኛ ነዳጅ የሚጠቀሙና እስከ 150 ሰው የመጫን አቅም ያላቸውን አውሮፕላኖችን ኢምብሬር እንደሚያመርት ተነግሯል፡፡
ከዚሁ ወሬ ጋር በተያያዘ ኢምብሬር በኢትዮጵያ በተለያዩ የአቪዬሽን ዘርፎች መሰማራት እንደሚፈልግ ለትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ ማስረዳቱ ተሰምቷል፡፡
ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ የብራዚል ምክትል አምባሳደር ጃክሰን ሊማን ጨምሮ የኩባንያው የስራ ኃላፊዎችን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፕላን ጥገና እና የአውሮፕላን አካል የማምረት አማራጮች አዋጭ የሆኑ ዘርፎች መሆናቸውን ሚኒስትሩ ለኢምብሬር ሃላፊዎች ነግረዋቸዋል፡፡
የኩባንያው ተወካዮች በበኩላቸየአውሮፕላን ጥገና፣ የአውሮፕላን አካላት ምርትና የስልጠና መስኮች ቀዳሚ የትብብር ፍላጎቶቻቸው እንደሆኑ በማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ለሀገር ውስጥ በረራ የሚያገለግሉትን አውሮፕላኖችን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከፍላጎት ባሟላ መልኩ ማቅረብ እንደሚችሉና ከአየር መንገዱ ጋርም በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ አንስተዋል ሲል የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስረድቷል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Comments