ሚያዝያ 16 2017 - በትግራይ ተፈናቃዮች ብዛት 1 ሚሊዮን የእምባ ጠባቂ ተቋም ተናገረ
- sheger1021fm
- Apr 24
- 1 min read
በትግራይ ክልል ያሉ ተፈናቃዮች ብዛት 1ሚሊዮን መድረሱንና ተፈናቃዮቹ ከዚህ ቀደም ከነበረው የከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን የእምባ ጠባቂ ተቋም ተናገረ፡፡
የተፈናቃዮቹ ችግር ከነበረው ተባብሶ ለበሽታና ለሞት እየተዳረጉ መሆኑን ከህዝብ #እምባ_ጠባቂ ተቋም የመቀሌ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሰምተናል፡፡

የቅርጫፍ ፅህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ፀሃዬ እምባዬ ምን አሉ? በትግራይ ክልል ያሉ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ በዚህ ዓመት በተቋሙ ቁጥጥር ተደርጎ የተፈናቃዮቹ ቁጥር 1ሚሊዮን መድረሱ ታውቋል፤ ዘንድሮ የሱዳኑን ጦርነት ሸሽተው የመጡ እንዲሁም ወደ ቀያቸው ተመልሰው የነበሩ ተፈናቃዮች፤ በተለያየ ምክንያት ወደ መጠለያዎቹ ዳግም የተመለሱ ተፈናቃዮች ቁጥር ሲደማመር ነው የተፈናቃዮቹ ብዛት 1 ሚሊዮን የደረሰው፡፡
ተፈናቃዮቹ የውሃ አቅርቦት የላቸውም፤ ከዚህ ቀደም በነብስ ወከፍ 15 ኪሎ ግራም እህል ይሰጣቸው ነበር አሁን ግን እርዳታው ወደ 9 ኪሎ ግራም ወርዷል፤ የምግብ እጥረቱ ያመጣቸው የተለያዩ በሽታዎች በመኖራቸው ነው፤በዚህም ምክንያት ሞት ተከስቷል ብለውናል አቶ ፀሃዬ፡፡
ተከስቷል ስለተባለው የሰዎች ሞት የጠየቅናቸው ሃላፊው ሞት መከሰቱን እናውቃለን ነገር ግን ስለ ጉዳዩ በዝርዝር እንዲነግሩን የክልሉን ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጠይቀናል ብለውናል፡፡
በቅርቡ በክልሉ የዘነበው ዝናብ የተፈናቃዮቹን መጠለያ ከጥቅም ውጭ አድርጎታል፤ተፈናቃዮቹ መጠለያ ድንኳን የላቸውም፡፡ መንግስት ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ነዋሪዎቹን ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል፡፡
በትግራይ ክልል ጠረፍ ባለው የኢሮብ አካባቢ ነዋሪዎች ላይ በኤርትራ ሰራዊት የሚደርሰው መሳደድ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የመቀሌ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሃላፊው ሰምተናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Comments