ብሔራዊ መታወቂያ የሌላችሁ የሀገር ልጆች በቀናችሁና በቀለላችሁ መንገድ የዲጅታል መታወቂያ ማግኘት ትችላላችሁ ተባለ።
ዛሬ ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ በብሔራዊ ደረጃ ማከናወን መጀመሩንም ሰምተናል።
የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባው የተጀመረው በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲሆን አዲስ አበባን ጨምሮ በ 29 ከተሞች በተመሳሳይ ግዜ ከዛሬ ጀምሮ መሰጠት ተጀምሯል።
በብሔራዊ ደረጃ ከሁለት ዓመት በኋላ 90 ሚሊዮን ሰዎች የዲጂታል መታወቂያ እንደሚኖራቸው እቅድ ተይዟል።
ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ ለ32 ሚሊዮን ዜጎች ምዝገባ ለማከናወን ማሰቡን ሲነገር ሰምተናል።
በዚህም ኩባንያው በወር በአማካኝ 1 ሚሊዮን ሰዎች ለመመዝገብ ማቀዱን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ አስረድተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ለዚሁ ስራ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአገልግሎት ማዕከላትን በመጠቀም እና የሰው ኃይል በማሰልጠን ስራውን አስጀምሯል ተብሏል፡፡
እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸው ዜጎች የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማከናወን ይችላሉ ሲባል ሰምተናል።
በኩባንያው የአገልግሎት ማዕከላት በአካል በመገኘት፤ ማንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እንደ ቀበሌ መታወቂያ፣ የታደሰ የመንጃ ፈቃድ፣ ፓስፖርት የመሳሰሉ ሰነዶችን በመያዝ ወይም የሰው ምስክር በማቅረብ በነጻ መመዝገብ ትችላላችሁ ተብላችኋል፡፡
ከከተማ እና የገጠር ነዋሪዎች በተጨማሪ የዩኒቨርስቲ፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና የብሔራዊ ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ተፈታኝ ተማሪዎች፣ በተለያዩ የተፈናቃዮች ጣቢያ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሕጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ያላቸው የውጭ ሃገር ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማከናወን እንደሚችሉ ሰምተናል፡፡
የዲጂታል መታወቂያ ከዜጎች በሚወሰዱ ውስን የባዮሜትሪክስ እና ዲሞግራፊክ መለያ አማካኝነት የተረጋገጠ መረጃ ለማቅረብ የሚያስችል መታወቂያ ነው።
ለቢዝነስ ትስስር፣ ለዲጁታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ ለቀለጠፈ ማህበራዊ አገልግሎት፣ ለተሻለ የዜጎች ህይወት እንዲሁም የሳይበር ማጭበርበርን በመከላከል አስተማማኝ የዲጂታል ሥነምህዳር ለመፍጠር ዲጂታል መታወቂያው የላቀ ሀገራዊ ፋይዳ ይኖረዋል ሲባል ሰምተናል፡፡
በኢትዮ ቴሌኮም የዳጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ዮዳሄ አርአያስላሴ፣ የሰነዶች ማረጋገጥ እና ምዝገባ ዋና ዳይሬክተር ሀሚድ ኪኒሶና ሌሎችም ተገኝተዋል።
የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን 4.6 ሚሊዮን ሰዎችአገልግሎቱን አግኝተዋል፡፡
ፕሮግራሙም ከተጀመረ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሆኖታል።
ተህቦ ንጉሴ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: @ShegerFMRadio102_1
Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comentarios