top of page

ሚያዝያ 10፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች

 

በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ያጋጠመ ከባድ የጎርፍ አደጋ ትናንት የአየር በረራውን በእጅጉ ያስተጓጎለ ነበር ተባለ፡፡

 

በከባድ ውሽንፍር የታጀበው ጎርፍ በዱባይ አለም አቀፍ ኤርፖርት ብቻ 290 አለም አቀፍ በረራዎችን እንዳሰረዘ ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

440 በረራዎች ደግሞ መዘግየት እንደገጠማቸው አድርጓል ተብሏል፡፡

 

መንገደኞችም ከፍተኛ መጉላላት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡

 

የኢሚሬትሱ ጎርፍ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

 

አንድ ግለሰብም ከነመኪናው በጎርፍ ተወስዶ ሕይወቱ ማለፉ ተሰምቷል፡፡

 

ሰሞኑን በኦማን ተከስቶ በነበረ ጎርፍም የ19 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ዘገባው አስታውሷል፡፡

 

#የፀጥታው ምክር ቤት

 

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በፍልስጤም የድርጅቱ ሙሉ አባልነት ጉዳይ ድምፅ ሊሰጥ ነው፡፡

 

ፍልስጤም የተባበሩት መንግስታት ሙሉ አባል ለመሆን የ5ቱን ቋሚ አባላት ጨምሮ የ9 የፀጥታውን ምክር ቤት አባል አገሮች ድጋፍ ማግኘት ይኖርባታል፡፡

 

አሜሪካ ፣ ብሪታንያ ፣ ሩሲያ ፣ ፈረንሳይ እና ቻይና ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል አገሮች ናቸው፡፡

 

አሜሪካ ግን ከወዲሁ የፍልስጤምን የተባበሩት መንግስታት ሙሉ አባልነት እንደማትቀበለው ፍንጭ እየሰጠች ነው፡፡

 

የፍልስጤም ጉዳይ በሌሎቹ አባል አገሮች ቢደገፍ እንኳ አሜሪካ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ እንደምታደርገው ተገምቷል፡፡

 

በአሁኑ ወቅት ፍልስጤም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያላት ቦታ የታዛቢነት እንደሆነ ሚድል ኢስት ሞኒተር አስታውሷል፡፡

 

 

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ኢራን ለሰነዘረችብን ጥቃት ምላሻችንን እንወስናለን አሉ፡፡

 

ኔታንያሁ እስራኤል ኢራንን መበቀሏ እንደማይቀር ፍንጭ የሰጡት ከብሪታንው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎርድ ካሜሩን ጋር በተነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡

 

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ራሳችንን ለመከላከልማ የምናደርገውን እናደርጋል ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

የብሪታንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለኔታንያሁ የእስራኤል ምላሽ እጥር ምጥን ያለ ሲሆን ይገባል እንዳሏቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

 

ኢራን ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሌሊት በእስራኤል ላይ ከ300 በላይ ሚሳየሎች እና ድሮኖችን ተኩሳለች፡፡

እስራኤል በብሪታንያ እና በሌሎም አጋሮቿ ድጋፍ ጭምር አብዛኞቹን የኢራን ሚሳየሎች እና ድሮኖች አምክኛቸዋለሁ ብላለች፡፡

 

ኢራን ደግሞ በእስራኤል ላይ በሰነዘርኩት ጥቃት ዓላማዬን አሳክቻለሁ እያለች ነው፡፡

 

 

በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በእስራኤል እና በፍልስጤማውያኑ የጦር ድርጅት (ሐማስ) መካከል የሚደረገው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ምንም እርምጃ አለማሳየቱን የካታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ፡፡

 

ድርድሩ ከተኩስ አቁም በተጨማሪ የታጋቾችን በፍልስጤማውያን እስረኖች መለዋወጥንም እንደሚጨምር የካታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሞሐመድ ቢን አብዱራህማን አል ታኒ ተናግረዋል፡፡

 

ዝርዝሩን ባያብራሩትም ድርድሩ ግን ፎቀቅ አላለም ማለታቸውን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡

 

አሁንም የተደራዳሪዎቹን አቋም ለማቀራረብ እየሞከርን ነው ብለዋል፡፡

 

ግብፅ እና አሜሪካም የአደራዳሪነት ሚና እንዳላቸው ተጠቅሷል፡፡

 

በእስራኤል እና በኢራን መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ በድርድሩ ላይ ማጥላቱን የካታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡

 

 

የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዓሊ አል ሳድቅ ከሀላፊነት መባረራቸው ተሰማ፡፡

 

ምክትላቸው ሆነው የቆዩት ሁሴን አዋድ ተክተዋቸው እንዲሰሩ መባሉን አናዶሉ ፅፏል፡፡

 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሀላፊነት መባረር በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን በተነበበ መንግስታዊ መግለጫ ዕወቁት መባሉ ተሰምቷል፡፡

 

ይሁንና ዓሊ ሳዲቅ ከሀላፊነቱ የተነሱበት ምክንያት በመግለጫው አልተጠቀሰም ተብሏል፡፡

 

ሱዳን በጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን በሚመራው ሉአላዊ ወታደራዊ ምክር ቤት እየተዳደረች መሆኑ ይታወቃል፡፡

 

የመንግስት ጦር በምህፃሩ RSF ከተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጋር ጦርነት ማካሄድ ከጀመረ ከአመት በላይ እንደሆነው ዘገባው አስታውሷል፡፡

 

 

የጀርመን የፀጥታ ሀይሎች በሩሲያ ሰላይነት የጠረጠሯቸውን ሁለት ግለሰቦች መያዛቸው ተሰማ፡፡

 

በሩሲያ ሰላይነት ተጠርጥረው የተያዙት ግለሰቦች የሩሲያም የጀርመንም መንታ ዜግነት ያላቸው እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

ተጠርጣሪዎቹ ጀርመን ወደ ዩክሬይን በምትልከው የእርዳታ የጦር መሳሪያ ጉዳይ አሻጥር ለመፈፀም እየዶለቱ ነበር ተብሏል፡፡

 

ከሁለቱ አንዱ ቀደም ሲል በምስራቃዊ ዩክሬይን ለትውልደ ሩሲያዎች ተሰልፎ ሲዋጋ እንደነበር በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

 

ጀርመን ለዩክሬይን ከፍተኛ የጦር መሳሪያ እርዳታ ከሚያቀርቡት አገሮች አንዷ ነች፡፡

 

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ አንስቶ ለዩክሬይን የ28 ቢሊዮን ዩሮ የዋጋ ግምት ያለው የጦር መሳሪያ እርዳታ መስጠቷን ዘገባው አስታውሷል፡፡

 

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

Telegram:  @ShegerFMRadio102_1

 

 

 

Comments


bottom of page