top of page

መጋቢት 9፣2016  - የመኮሮኒ እና የፓስታ ዋጋ በቅርቡ ሊቀንስ ይችላል ተባለ

ዋጋቸው አልቀመስ እያለ የመጣው የመኮሮኒ እና የፓስታ ዋጋ በቅርቡ ሊቀንስ ይችላል ተባለ፡፡

 

ይህን የተናገረው የኢትዮጵያ የዱቄት አምራቾች ማህበር ነው፡፡

 

ዛሬ የዱቄት፣ የስንዴና የዘይት አምራቾች ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከሚመለከታቸው ጋር ሲመክሩ ውለዋል፡፡

 

አንድ ኩንታል ዱቄት ከ6,800 ወደ 5,800 ዝቅ እንዲል መደረጉና በኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ እና ማስተካከያዎች በመደረጉ ዋጋው እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡

 

ማህበሩ ከጂ አይ ዜድ ጋር እና ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን ባደረገው ጥናት በአምራቾቹ ያሉበትን ችግሮችና ፈተናዎች ለይተዋል፡፡

 

ኢንዱስትሪው ችግሮቹና እድሎቹ ምንድናቸው? በገበያ ውስጥ የምግብ ማረጋጋቱን ሚና አምራቾቹ እንዴት ማገዝ አለባቸው? በሚለው ጉዳይ ላይ ተመክሯል፡፡

 


ማህበሩ ባደረገው ጥናት የዱቄትና የዱቄት ምርት ማቀነባበሪያዎች እንደ ፓስታና መኮሮኒ እንዲሁም ብስኩት ላይ ያለውን ቫት ወይም ተጨማሪ እሴት ታክስ አሁንም እንዲነሳ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

 

የገንዘብ ሚኒስቴር ቀድሞውኑ በስንዴ ዱቄት ላይ 25 በመቶ ጥሎት የነበረውን ታክስ በማንሳቱ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የስንዴ ምርትና ውጤቶች  በገበያው ላይ ቀንሶ ታገኙታላችሁ ተብሏል፡፡

 

በሌላም በኩል ብስኩት ላይ ተጥሎ የቆየው ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲነሳ ተጠይቋል፡፡

 

በዚሁ ምክክር ላይ ያልተገደበና መጠኑ ያልታወቀ የስንዴ ዱቄት ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ነው ተብሏል፡፡

 

ይህም የሀገር ውስጡን አምራቾች አደጋ ላይ ጥሏቸዋል ተብሏል፡፡

 

ለአገር ውስጥ ግብአት የሚሆነው የአኩሪ አተር በገፍ ወይም በብዛት ወደ ውጪ መላክ አገር ውስጥ ላሉ ማቀነባበሪያዎች ፈተና መሆኑንም ሰምተናል፡፡

 

በኢንዱስትሪው ላይ ከግጭት ጋር እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ከገበያው ወጥተው የነበሩ የዱቄት አምራቾች ሊመለሱ ይችላሉ ተብሏል፡፡

 

የገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ፖሊሲ ዳይሬክተር አቶ ሙላይ ወልዱ  በስንዴ ዱቄት ላይ የነበረው ታክስ መሻሻሉን አረጋግጠዋል፡፡

 

በብስኩትን ተያያዥ ምርቶች ላይ ያለውንና የቀረበውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ጥያቄዎች በተመለከተ ደግሞ በቅድሚያ ጉዳዩን መፈተሽና ማጥናት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

 

 

ተህቦ ንጉሴ


 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

Comments


bottom of page