top of page

መጋቢት 8 2017 - በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በሚደርስ ስርቆት አጥፊዎችን በመቅጣት ረገድ ክፍተት መኖሩ ተሰማ

  • sheger1021fm
  • Mar 17
  • 2 min read

በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በሚደርስ ስርቆት ከፍተኛ ሀብት እየባከነ ቢሆንም አጥፊዎችን በመቅጣት ረገድ ክፍተት መኖሩ ተሰማ፡፡


በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም #ስርቆት ካለፉት ዓመታት አንፃር እየቀነሰ ቢሆንም ችግሩ ግን አሁንም በስፋት አለ የሚለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ነው፡፡


በመሰረተ ልማቶቹ ለላይ ጉዳት ያደረሰ ወይም ስርቆት የፈፀመ ማንኛውም ግለሰብ የእስር እና የገንዘብ ቅጣት የሚቀጣበት ህግ ቢኖርም ለፍርድ የሚቀርቡት ጥቂቶቹ ናቸው ተብሏል፡፡


በማህበረሰቡ በኩል ለተቋሙ የሚደርሱ ጥቆማዎችን በመከታተል ውሳኔ እንዲሰጥባቸው እናደርጋለን የሚሉት የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ታዬ ከሚደርሰው ጥፋት አንፃር ግን ወንጀሉን ፈፅመው በቁጥጥር ስር የማይውሉት ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም ብለውናል፡፡


በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት የደረሰው ጉዳት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሀይልና የመሰረተ ልማት ስርቆት ተፈፅሟል ተብሏል፡፡


በዚህም በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት የኃይልና ሌሎች መሰረት-ልማት ሥርቆት ፈፅመው በ #ፍርድ_ቤት በተረጋገጠባቸው 11 የወንጀል ክሶች 13 ተከሳሾች ከሁለት ወር ቀላል እስራት እስከ 10 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲፈረድባቸው ማድረግ ተችሏል ብለውናል፡፡

በተጨማሪም ተከሳሾቹ ላይ 50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት መጣሉ የነገሩን ስራ አስፈፃሚው በሌሎች ተጠርጣሪዎች ክስ ተከፍቶ በክትትል ላይ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡


ጥፋቱ የሚፈፀመው ከማህበረሰቡ ውስጥ ስለሆነ ከዚያ ከሚገኘው መረጃ ተነስተን ክትትል ካላደረግን ወንጀለኞቹን በተቋም በኩል ልናውቅ አንችልም የሚሉት አቶ መላኩ ስርቆት የሚፈፁሙ ግለሰቦችን ነዋሪው ባለመጠቆሙ ለዚህ ችግር እንድንጋለጥ አድርጎናል ብለዋል፡፡


በሌላ በኩል መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት ከተፈፀመ በኋላ የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉ ሆነው አስቀድሞ የመከላከል ስራ ከህግ አካላት ጋር እየተሰራን ነው ነገር ግን ማህበረሰቡም ለዚህ ተባባሪ ሊሆን ይገባዋል ብሏል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፡፡


በተጨማሪም በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም ስርቆት ከጊዜ ወደ ጊዜ የመቀነው ቢሆንም ችግሩ ግን አሁንም አገልግሎቱን እየፈተነው መሆኑን ሰምተናል፡፡


እንደማሳያም ባለፉት ሰባት ወራት በመቐሌ እና በሽረ ሪጅን በተፈፀመ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት ከ24 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት እንደደረሰበት ተናግሯል፡፡


በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በበጀት አመቱ 7 ወራት በትራንስፎርመር፣ በኃይልና የኤሌክትሪክ ሽቦዎች ላይ በተፈፀመ ስርቆት ከ50 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኃይልና መሰረተ-ልማት ሰርቆት ተፈፅሞበታል፡፡


በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በሚፈፀም ስርቆት ሀይል በመቆረጥም ሆነ በሌላ ሌላውም ቀዳሚ ተጎጂ ማህበረሰቡ ቢሆንም ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይልም ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚያጋጥመው የሚናገሩት የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ታዬ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓት በውጭ ምንዛሪ የሚመጣ በመሆኑ ከፍተኛ ጫና ያሳድርብናል ብለዋል፡፡


ከ54 በመቶ ያልዘለለውን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ቁጥር ለመጨመርም አገልግሎቱ ሊሰራቸው ያቀዳቸውን አዳዲስ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በመተው በስርቆት የወደሙት ላይ የሚያወጣው ወጭም ቀላል አለመሆኑ ተነግሯል፡፡





ፋሲካ ሙሉወርቅ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page