መጋቢት 30 2017 - ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዘዳንት ሆነው ተሰየሙ፡፡
- sheger1021fm
- Apr 8
- 2 min read
ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዘዳንት ሆነው ተሰየሙ፡፡
ዛሬ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሬዘዳንት ርክክብ ሥነ-ሥርዓት መካሄዱን እና አቶ ጌታቸው ረዳ ለሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ስልጣን በሰላማዊ መንገድ ማሸጋገራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናግረዋል፡፡
በይፋዊ ማህበራዊ ትስስር ገፃቸው እንዳሉት ጀነራል ታደሰ ባለፉት 2 ዓመታት የአቶ ጌታቸው ምክትል ሆነው ያገለገሉ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡

በተጠቀሱት ዓመታት የነበሩትን ድካሞችን እና ጥንካሬዎችን የሚገነዘቡ ሰው መሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
አሁን በትግራይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ወደፊት ሊወስዱ ይችላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው እና የትግራይ ህዝብ የተጠማውን ሰላምና ልማት ለማሳካት ታሪክ የሰጣቸውን እድል ይጠቀሙበታል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡
ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ የቃል ኪዳን ሰነድ በመፈረም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ሆነው ስራ ጀምረዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬቸው የመመለስ ሂደት፤ በጅምር ያለው ስራ እንዲጠናቀቅ እና በቀሪ አካባቢዎችም በፍጥነት እንዲተገበር ማድረግ በቃል ኪዳን ሰነዱ ከተካተቱ ሃላፊነቶች የመጀመሪያው ነው።
በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ትጥቅ የመፍታት እና የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ ማድረግ ሌላው ሆኖ በቃል ኪዳን ሰነዱ ተጠቅሷል።
በክልሉ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ ፤ ለህዝብ ደህንነት ፤ ለሰላም እና ፀጥታ ጠንቅ የሆኑ ጉልህ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ ፤ ለዚህ ተገቢውን የህግ የቁጥጥር እና የህግ ማስከበር ስራ መስራትም ጄኔራል ታደሰ እንዲወጧቸው ተብሎ በቃል ኪዳን ሰነዱ የሰፈሩ እና የፈረሙባቸው ጉዳዮች ናቸው።
መደበኛ የልማት ስራዎች ፤ መንግስታዊ እና ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲሁም የመልሶ ግንባታ ስራዎች እንቀላጠፉ ማድረግ ፤ ከህገ መንግስታዊ እና ህጋዊ ስርአት ፤ ከሀገር ሉዓላዊነት እና ፕሪቶሪያ ስምምነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ ደግሞ ሌሎቹ ናቸው።
ክልሉ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ ፤ በክልሉ የሲቪክ እና የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ የሆኑበት ፤ የፖለቲካ ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ዐውድ እንዲፈጠር መስራትም ጀነራል ታደሰ እንዲወጧቸው ተብለው በቃል ኪዳን ሰነዱ ከተጠቀሱ ሃላፊነቶች መካከል ይገኙባቸዋል።
የክልሉ ህዝብ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ተዋንያን በአገራዊ የምክክር ሂደት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና የክልሉ መንግስታዊ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን እንቅስቃሴዎች የአገሪቱን ህዝቦች ትስስር እና መልካም ግንኙነት በሚያጠናክሩ ፤ ህግና ህገ መንግስታዊ ሥርዓትን የሚያስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥም የአዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሃላፊነት ሆኖ በቃልኪዳን ሰነዱ ሰፍሯል፡፡
የጊዜያዊ ፕሬዘዳንቱ ፕሬዘዳንት ሆነው የተሰየሙት ሌተና ጀነራል ታደሰም እንደሚያሳኳቸው ተስማምተው ፈርመዋል ተብሏል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
📌Spotify : https://shorturl.at/QG8f2
Comments