top of page

መጋቢት 3 2017 - የወንዞች ዳርቻን ለማልማት እና ብክለትን ለመከላከል የወጣው ደንብ ቅጣት ላይ ያተኮረ ነው የሚል ትችት ቀረበበት

የአዲስ አበባን ወንዞች ዳርቻን ለማልማት እና ብክለትን ለመከላከል ተብሎ የወጣው ደንብ ከማስተማር ይልቅ ቅጣት ላይ ያተኮረ ነው የሚል ትችት ቀረበበት፡፡


የከተማዋ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በበኩሉ ቅጣቱ ከጥፋቱ ጋር ሲነጻጻር ያንሳል ብሏል፡፡


በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የጸደቀው የወንዝ ዳርቻ ልማት እና ብክለትን መከላከል ደንብ ማንኛውም በካይ ፍሳሾችን እና ቆሻሻን ወደ ወንዞች የሚጥል፣ የሚያከማች እና የሚለቅን ግለሰብን እንዲሁም ተቋምን ከ 1 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር እንዲቀጣ የሚያዝ ነው፡፡


የደንብ ማስከበር ባለስልጣን 6,000 የሚሆኑ ደንብ አስከባሪ ሰራተኞቼን ወደ ወንዞች በካይ ፍሳሾችን የሚለቁ እና ቆሻሻዎችን የሚጥሉ ግለሰቦችን እና ተቋማትን እየፈለጉ እንዲቀጡ አሰማርቻለው ብሏል፡፡


ለምሳሌ በባህሪው አደገኝነት ያለው ደረቅም ይሁን ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዞች የለቀቀ ወይንም የጣለ ግለሰብ ከሆነ 500 ሺህ ብር ተቋም ከሆነ ደግሞ አንድ ሚለዮን ብር እንዲቀጣ ደንግጓል፡፡

በደንቡ ለወንዝ ዳርቻው ልማት አስፈላጊ ከሆነ ግንባታ ወጪ የፕላስቲክ ቤት ወይንም ማንኛውም ግንባታ መገንባት ደግሞ 200 ሺህ ብር ያስቀጣል፡፡


አትክልት ፍራፍሬዎችን እና ተረፈ ምርቶችን ወደ ወንዞች የጣለ ግለሰብ 20 ሺህ ብር እንዲቀጣ የደነገገው ደንቡ ከመኖሪያ ቤት፣ የሽንት ቤት ቱቦ አልያም ያልተጣራ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዞች የለቀቀ ግለሰብ ደግሞ 150 ሺህ ብር እንዲቀጣ ያዛል፡፡


ታድያ ይህ ደንብ የያዘው ቅጣት የተጋነነ ነው፣ ቅጣት ላይ ያተኮረ፣ የህብረተሰቡንም የመክፈል አቅም ያላገናዘበ ነው የሚል ቅሬታ እና ትችት ከከተማዋ ነዋሪዎች ቀርቦበታል፡፡


ቅሬታው የቀረበው የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና የከተማው የደንብ ማስከበር ባለስልጣን በትናንትናው እለት በከንቲባ ጽ/ት ከኢንዱስትሪ፣ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ጋር እና ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በደንቡ ላይ በተደረገ ወይይት ላይ ነው፡፡


ሃጂ ኪነዱ ካሲም የተባሉ የውይይቱ ተሳታፉ «በቅጣት ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም እኔ ቅጣት አብዛኛው ይበልጥ ምሬትን ያመጣል የሚሰራውን ልማት በጭፍን እንዲታይ የሚደርግ ነው የሚሆነው» ብለዋል፡፡

ማህሌት ዐቢይ የተባሉ ሌላ ተሳታፊ በበኩላቸው የወንዝ ዳርቻ ኗሪ መሆናቸውን በመጠቆም ገባር ወንዞች ከላይ ቆሻሻቸውን ይዘው መጥተው ነው እኛ ጋር የሚጥሉት የምንጠይቀው ግን እኛ ነን ምን እናድርግ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡


ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የከተማዋ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሺህ አለቃ ዘሪሁን ተፈራ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየተሰራ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡


ግንዛቤ ማስጨበጡ ስራም አጥፊዎችን የመቅጣቱ ሁኔታ ይቀጥላል ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ ለዚህም የባለስልጣኑ 6000 የሚሆኑ ሰራተኞች አጥፊዎችን እንዲቀጡ በወንዞች ወስጥ ተሰማርተዋል ብለዋል፡፡


የከተማዋ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ከሌላ ቦታ ቆሻሻ እያመጡ እናንተ ጋር ሲጥሉ እናንተ እንዳትቀጡ አስቀድማቹ መጠቆም አለባቹ ብለዋል፡፡


የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ደሪባ በበኩላቸው «ገንዘቡ ተሰርቶ ይመጣል የሰው ልጅ እንዴ ካለፈ ግን ተመልሶ አይመጣም ከከተማዋ ተሰብስቦ የሚወጣው የሚሄደው ህብረተሰብ ላይ ነው ፍሳሹ ቆሻሻው የሚከትለው የጤና ችግር ከቅጣቱ አንጻር ዝቅተኛ ነው» ብለዋል፡፡


በአዲስ አበባ ያሉ 76 ወንዞች የተበከሉ ናቸው ተብሏል፡፡


ያሬድ እዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


Komentar


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page