ኢትዮጵያ ከምንም ጊዜ በላይ ሰላም የሚያስፈልጋት ወቅት ላይ ትገኛለች፤ ችግሮችንም በንግግር ሊፈቱ ይገባል ተባለ።
በአማራ ክልል ያለውን የትጥቅ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እና በውይይት ቢፈታ የሚኖረው ፋይዳ ላይ ያተኮረ ዉይይት ዛሬ በአዲስ አበበ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ የሰላም ተቋም የቦርድ ሊቀመንበር ሙሉጌታ ኢተፋ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከምንም ጊዜ በላይ ሰላም የሚያስፈልጋት ወቅት ላይ ናት ብለው ሲናገሩ ሰምተናል፡፡
ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ወቅት ላይ ትገኛለች፤ ልጆቿም ከምንም ጊዜ በላይ ሰላምን በሚፈልጉበት ታሪካዊ ወቅት ላይ ናቸው ያሉት ዶ/ር ሙሉጌታ እስከ መቼ እናቶች እና አባቶች በልጆቻቸው ተስፋ ሳይሆን ሞት እና አካል መጉደል እያለቀሱ እያዘኑ እና ጧሪ ቀባሪ እያጡ ይኖራሉ ሲሉም ጠይቀዋል።
![](https://static.wixstatic.com/media/b24dd6_7010e02464324d5396ba2a9d04c95b41~mv2.jpg/v1/fill/w_980,h_735,al_c,q_85,usm_0.66_1.00_0.01,enc_auto/b24dd6_7010e02464324d5396ba2a9d04c95b41~mv2.jpg)
ኢትዮጵያ ይህን የልጆቿን ሕይወት የሚነጥቅ ሃብቷን የሚያጠፋ እና ለልማት ተብለዉ የተገነቡ መሰረት ልማቶችን እያወደመ ያለዉን ግጭት በንግግር መፍታት አለባትም ብለዋል፡፡
ይህን ግጭት ዛሬ ማቆም የማንችል ከሆነ፤ ጥፋቱም እንዲቀጥል ከፈቀድን እያንዳንዳችን ከታሪክ ተወቃሽነት አናመልጥም ሲሉ የቦርድ ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል።
ግጭቶች እንዳይከሰቱ ቀድሞ መከላከል፣ ከተከሰቱም የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ መፍትሔ መስጠት በመንግስት ብቻ የሚቻል ስላልሆነ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ እና ሌሎችም ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ፤ ከሰሜኑ ጦርነት መማር አልተቻለም ያሉ ሲሆን ሰላምን ማምጣት ደግሞ መንግስት ብቻ የሚችለው ሳይሆን የሁሉን ድርሻ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የዲሞክራሲና አስተዳደር ቢሮ ዳይሬክተር እስቴቭኒ ጋርዴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች የከፋ ጉዳት እያስከተሉ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአማራ ክልል ያለው ግጭትም ት/ቤቶች እና የጤና አገልግሎቶች ላይ የከፋ ጉዳት አድርሰዋል ተብሏል፡፡
![](https://static.wixstatic.com/media/b24dd6_d48eccca0cd64334bee2f9b0a2e83c6b~mv2.jpg/v1/fill/w_980,h_735,al_c,q_85,usm_0.66_1.00_0.01,enc_auto/b24dd6_d48eccca0cd64334bee2f9b0a2e83c6b~mv2.jpg)
መንግስት ለንግግር ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዉ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም እና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት(USAID) በመተባበር መድረኩ መዘጋጀቱን ሰምተናል፡፡
የመድረኩ ዋንኛ አላማ በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት በእዉነተኛ ውይይት ለመፍታት እየተደረጉ ያሉትን ጥረቶች መደገፍ ነዉ የተባለ ሲሆን በክልሉ የተከሰተዉ ግጭት በንግግር ቢፈታ ሊገኙ የሚችሉ ጥቅሞችን ለህዝብ ይፋ ማድረግ ነዉ ተብሏል።
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Commentaires