መጋቢት 27፣2016 - የምክክር ኮሚሽን በ800 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ አጠናቅቄአለሁ አለ
- sheger1021fm
- Apr 5, 2024
- 1 min read
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ800 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ አጠናቅቄአለሁ አለ፡፡
በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ ደግሞ 100 ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ አጠናቅቃለሁ ብሏል፡፡
ኮሚሽኑ ይህን ያለው ሊሰራቸው ባቀደውና በሰራቸው ስራ ዙሪያዎች ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡
ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ናቸው፡፡
70 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ አካባቢዎች የተሳታፊ ልየታ ተጠናቋል ብለዋል፡፡
የተሳታፊ ልየታ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀባቸው ክልሎች መኖራቸውንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

ክልሎቹም አፋር ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ፣ ጋምቤላ ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ የተደረገባቸው ቦታዎች መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ኮሚሽኑ በሶማሌ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል የተሳታፊ ልየታ በማጠናቀቅ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ትግራይና አማራ ክልል ደግሞ የተሳታፊ ልየታ ስራ ያልጀመርኩባቸው ናቸው ብሏል፡፡
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ያለውን ተቀባይነት በተመለከተ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የኮሚሸኑ ቃል አቀባይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ነገሮችን እስከማስተካክል ትንሽ ታገሱን የሚል ምላሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ውስጥ ያሉ አካላትን በምክክሩ ለማካተት ምን እየተሰራ ነው የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበት ዓላማ የማደራደርና የማስታረቅ አይደለም፤ ይሁንና ግን ሁሉም አካላት በምክክሩ ሁሉም እንዲካፈሉ የተቻለኝን እያደረኩ ነው ማለቱን ለመገናኛ ብዙሃን ተናግሯል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
ShegerFM: @ShegerFMRadio102_1
Comments