መጋቢት 25 2017 - ታሪክን የኋሊት - የሰብአዊ መብት ታጋዩ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር
- sheger1021fm
- Apr 3
- 2 min read
የሰብአዊ መብት ታጋዩ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር “ወደ ተራራው ጫፍ ወጣሁ” የሚለውን ታሪካዊውና የመጨረሻውን ንግግሩን ያደረገው ፣ በ1960 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡
ከዚያ ንግግሩ 24 ሰዓታት በኋላ ተገደለ፡፡
ማርቲን ሉተር በሜምፊስ ተገኝቶ አስደናቂ የተባለውን ንግግር ያደረገው ፣ ጥቁር የፅዳት ሰራተኞች የጀመሩትን የስራ ማቆም አድማ ለማገዝ ነበር፡፡
ማርቲን ሉተር ፣ የአሜሪካ ጥቁሮች ፣ የእኩልነት መብታቸው እንዲከበር መስዋዕትነትን የጠየቁ አታካች ትግሎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
የባፕቲስት ቄስና የፖለቲካ ፈላስፋ የነበረው ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ እድሜ ልኩን የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ሆኖ የኖረና ለእስርና ለቅጣት ሲዳረግ የቆየ ነው፡፡
የጥቁሮች የመምረጥ ፣ የሰራተኞች የሰብአዊ መብት እንዲከበር የተቃውሞ ሰልፎችን ፣ የስራ ማቆም አድማዎችን አስተባብሩዋል ፣ ተሳትፏል ፤ ውጤት አስገኝቷል፡፡

እጅግ አነቃቂ ፣ መሳጭና ጀር ገብ በሆነው የንግግር ችሎታው በርካታ ተከታዮች ያፈራው ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ለጥቁሮች እኩልነት ዋሽንግተን በተደረገ ታላቅ ሰልፍ “ሕልም አለኝ” የሚለው ንግግሩ እስከ ዛሬም በድናቆት ይታሰባል፡፡
ይሁንና የሉተር እንቀስቃሴ በመንግስትና በፅንፈኛ ነጮች ዘንድ አልተወደደለትም፡፡
እስራትና ማስፈራራት የየእለት ገጠመኙ ነበር፡፡
ኤፍ ቢ አይ ሁልጊዜ ይከታተለው ነበር፡፡
ሉተር ፣ማኔፌስ ከሰዓት በኋላ ደርሶ ፣ ያደረገው በግለት የተጓዙ ንግግሩ፣ ሞቱ እንደታቀረበ የሚጠቁም ነበር፡፡
“አሁን ምን እንደምሆን አላውቅም አስቸጋሪ ቀናት ከፊታችን ተደቅነዋል፣ ግን የሚያሳስበኝ አይደለም ፡፡
ምክንያቱም በተራራው ጫፍ ላይ ነኝ፡፡ እና አያስጨንቀኝም፡፡
እንደማንኛውም ሰው ረጅም እድሜ መኖር እፈልጋለሁ፡፡ ግን አሁን ስለዚያ አላስብም ፣ እግዚአብሔር የፈቀደውን ለመስራት እፈልጋለሁ ፡ ወደ ተራራው ጫፍ እንድወጣ ፈቅዶልኛል፡፡ እና የተስፋይቱን ሃገር አይቻታለሁ፡፡ ከእናንተ ጋር ላልዘልቅ እችላለሁ፡፡
ግን በዚች ምሽት ላሳውቃችሁ የምፈልገው እንደሕዝብ ወደተስፋይቱ አገር እንደርሳለን፡፡ ስለምንም ነገር አልጨነቅም ፡፡ ማንንም አልፈራም፡፡
“ዓይኖቼ የአምላክን ታላቅነት አይተዋልና ፤” ይህንን ንግግር ለደጋፊዎቹ ካደረገ 24 ሰዓት በኋላ ባረፈበት ሆቴል በረንዳ ላይ እንደቆመ በ39 አመቱ በጥይት ተገደለ፡፡በአብዛኛው አሜሪካ የጥቁሮች አመፅ ተቀሰቀሰ፡፡
ሉተር ውጤቱን ሳያይ ቢገደልም ሲታገልለት የኖረው የጥቁሮች መብት ተከብሩዋል፡፡
ለፕሬዘዳንትነትም ለመመረጥና በከፍተኛ የስልጣን እርከን ለመመደብ በቅተዋል፡፡
ሉተር ያደረገው ተጋድሎ ዕውቅና አግኝቶ ፣ የልደቱ ቀኑ ብሔራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበርና የፕሬዝዳንቱን ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡
ማርቲን ሉተር ታሪካዊ የተባለውን የመጨረሻውን ንግግር ካደረገ 57 ዓመት ሞላው፡፡
እሸቴ አሰፋ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
📌Spotify : https://shorturl.at/QG8f2
Commentaires