top of page

መጋቢት 25፣2016 - በትግራይ ክልል በትምህርት ገበታ ላይ ያለው የተማሪ መጠን 41 በመቶ ብቻ ነው ተባለ

በትግራይ ክልል በትምህርት ገበታ ላይ ያለው የተማሪ መጠን 41 በመቶ ብቻ ነው ተባለ፡፡


ይህን ያለው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ነው፡፡


በክልሉ 2.4 ሚሊዮን ተማሪ በትምህርት ገበታ ላይ መኖር ነበረበት አሁን ያለው ተማሪ ግን 994 ሺህ 369 ተማሪ ብቻ ነው፤ ይህም 41.1 በመቶ ነው ብሏል ጽ/ቤቱ፡፡

ምክንያቱም ደግሞ የሰሜኑ ጦርነት እንደሆነ ጽህፈት ቤቱ አስረድቷል፡፡


ጽ/ቤቱ በ22 ወረዳዎች በሚገኙ 794 ትምህርት ቤቶች ላይ በተደረገ ክትትል 112 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ 595 በከፊል እንደተጎዱ አስረድቷል፡፡


ከ795 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ምንም ዓይነት ጉዳት ያልደረሰባቸው 47 ትምህርት ቤቶች ብቻ እንደሆኑ ተናግሯል፡፡

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በክልሉ ርዕሰ ከተማ መቀሌ ባደረኩት ክትትልም በ24 ትምህርት ቤቶች ተፈናቃዮች መኖራቸውን አረጋግጫለው ብሏል፡፡


ይህ ማለትም ካሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁሉም ላይ ማለት በሚባል ደረጃ ተፈናቃዎች አሉ ያሉን የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ጸሃዬ አንባዬ ናቸው፡፡


በፊት በወረዳ እና በፌደራል መንግስት ለትምህርት ቤቶች ይሰጥ የነበረው ድጎማም አሁን የለም ብለዋል ሃላፊው፡፡

በክልሉ የመምህራን እጥረት እንዳለም ሃላፊው ነግረውናል፡፡


ያሉትም መምህራን ቢሆኑ የ17 ወር ውዝፍ ደሞዝ ስላተከፈላቸው በስራቸው ደስተኛ ሆነው እየሰሩ እንዳል ሆነ እና በዚህም የመማር ማስተማር ሂደቱ ጥራት የጎደለው እንዲሆን አድርጎታል ተብሏል፡፡


ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የወደሙትን ትምህርት ቤቶች ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ የትምህርት ግብዓቶችን ማሟላት እና በስራ ላይ ያሉ መምህራን ደስተኛ ሆነው እንዲሰሩ ውዝፍ ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው በምክረ ሀሳብ አስቀምጧል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





ShegerFM: @ShegerFMRadio102_1

Comentarios


bottom of page