top of page

መጋቢት 25፣2016 - ለአፓርትመንትና ለጋራ መኖሪያ ቤቶች አማካኝ የሽያጭ ዋጋ ተመን በ34 በመቶ እንዲቀንስ ተደረገ

በአዲስ አበባ ለአፓርትመንት ቤቶች እና ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ወይም ኮንዶሚኒየም ቤቶች አማካኝ የሽያጭ ዋጋ ተመን በ34 በመቶ እንዲቀንስ ተደረገ፡፡


ይህን ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ነው።


ቢሮው ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ለሁሉም ክ/ከተሞች የፃፈውን የአፈፃፀም መመሪያ ሸገር ተመልክቶታል።


በከተማዋ የቤት ሽያጭ ዋጋ ተብሎ በገዥና ሻጭ መካከል የሚደረግ ውል ላይ የሚቀርበው ዋጋ እጅግ በተጋነነ መልኩ ዝቅተኛ በመሆኑ እና በባለሙያ የሚወሰድ የቤት ግምት ዋጋ ወቅታዊ ባመሆኑ መንግስት ከቤት ሽያጭ ተገቢውን ገቢ እየሰበሰበ እንዳልነበረ ቢሮው አስታውሷል፡፡


ይህንን ችግር ለመፍታት እንዲቻል ካለፈው ዓመት ሰኔ 8፣2015  ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ወቅታዊ የቤት ሽያጭ ዋጋ  ተግባራዊ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡


ይሁን እንጂ በከተማ ደረጃ ተጠንቶ ተግባራዊ የተደረገ የቤት ሽያጭ ዋጋ እና አሰራሩ ላይ ከህብረተሰቡ በርካታ ቅሬታዎች እየቀረቡ በመሆኑ በመሬት ልማትና አስተዳደተር ቢሮ እና የመሬት ይዞታ ምዝገበና መረጃ አጄንሲ በጋራ ጥናት በማድረግ የተለዩ ክፍተቶችና እና የቤት ሽያጭ ግምት ላይ ማሻሻያ ተደርጓል ተብሏል።


በተደረገው ማሻሻያም ለአፓርትመንት ቤቶች እና ኮንዶሚኒየም ቤቶች  የሽያጭ ዋጋ ተመን አምና በሰኔ ወር ከነበረው 34 በመቶ እንዲቀንስ ተደርጓል።


በተሻሻለው  የቤት ሽያጭ ዋጋ ተመን መሰረት ከኮንደሚንየም እና አፓርትመንት ውጪ ለሆኑ ግንባታዎች፦


● የግንባታ ነጠላ ዋጋ በጭቃ የተሰራ ቪላ ቤት (G+0) ነጠላ ዋጋ በካሬ 15,000 ብር፣

● በብሎኬት የተሰራ የቪላ ቤት (G+0) ነጠላ ዋጋ በካሬ 20,000 ብር፣

● የህንጻ ወለላቸው ከG+1 እስከ G+5 25,000 ብር እና፣

● G+6 እና በላይ የሆኑ ቤት ወይም ህንጻ ነጠላ ዋጋ በካሬ 30,000 ተደርጓል፡፡


የቦታው መገኛ ዋጋ('location value') ለከተማው የቦታ ደረጃ የጸደቀው ወቅታዊ አማካይ የሊዝ ጨረታ ዋጋ እንዲሆን መደረጉንም ተመልክተናል።


የቤት ስም ንብረት ዝውውር ክፍያ ማለትም አሹራ 4 በመቶ እና የቴምብር ቀረጥ 2 በመቶ ከጠቅላላ የቤቱ ሽያጭ ዋጋ ተሰልቶ ከ ከመጋቢት17፣2016 ዓ/ም  ጀምሮ እንዲከፈልም ቢሮ አዟል።


ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር  ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የቤት ሽያጭ ዋጋ ተመን መሻሩንም ቢሮ ጠቅሷል።


በፍርድ ቤት እና በባንክ ሃራጅ ሽያጭ የስም ንብረት ዝውውር የሚጠየቅባቸው ይዞታዎችን በተመለከተ ይዞታ አገልግሎትና መብት ፈጠራ ደንብ ላይ በተቀመጠው አግባብ ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።


ይህ ማሻሻያ መምሪያ ከመውጣቱ በፊት የስም ንብረት ዝውውር አገልግሎት ጠይቀው በሂደት ላይ ሆኖ ክፍያ የፈጸሙ ተጋልጋዮች በቀድሞ አሰራር በከፈሉት ክፍያ መሰረት ይስተናገዳሉ ያለው ቢሮው ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ ህንፃዎች የትመና ስራ የሚሰራላቸው ግንባታው በደረሰበት ወይም አሁን ላይ ባለበት ግንባታ ደረጃ ይሆናል ብሏል፡፡


ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
תגובות


bottom of page