top of page

መጋቢት 23 2017 - ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት፤ ከ9 ወር በፊት ከነበረበት በ200 በመቶ መጨመሩ ተናገረ

  • sheger1021fm
  • Apr 1
  • 2 min read

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት፤ ከዘጠኝ ወር በፊት ከነበረበት ጋር ሲነፃፀር 200 በመቶ መጨመሩ ተናገረ፡፡


የመጠባበቂያ ክምችቱ #የውጭ_ምንዛሪ ተመን በገበያው እንዲወሰን ከተደረገበት ሀምሌ 22/2016 ዓ.ም ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን፤ በበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ ሶስት ወራት እየቀሩ እቅዱ መሳካቱን የተናገሩት የብሔራዊ ባንኩ ዋና ገዥ ማሞ እስመለአለም ምህረቱ ናቸው፡፡


ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወዲህ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ለረጅም ዐኣመታት ስር ሰዶ የቆየውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሂደት መሰረታዊ በሚባል ደረጃ እየተቃለለና ፍሰቱም እየጨመረ ይገኛል ብለዋል፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በትናንትናው እለት ከባንክ ስራ አስፈፃሚዎች ጋር በአጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደርና አፈፃፀም በተመለከተ ውይይት ማድረጉንም ገዢው አስረድተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በአፈፃፀም በኩል የሚታዩ አንዳንድ ችግሮች እንዲስተካከሉ እና የውጭ ምንዛሪ መመሪያዎች በጥብቅ እንዲፈፀሙ መመሪያ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡


በተለይም ባንኮች የሚያስከፍሉትን ኮሚሽን እና የአገልግሎት ክፍያ ተመጣጣኝ እንዲያደርጉ መመሪያ ሰጥቷል ተብሏል፡፡


በየሁለት ሳምንቱም የውጭ ምንዛሪ ግልፅ ጨረታ ቢያንስ የተያዘው በጀት መጨረሻ ድረስ እንደሚወጣም አቶ ማሞ ጠቅሰዋል፡፡


ውጭ ምንዛሪ ግብይት ከባንክ ሥርዓት ውጪ በሚያካሂዱ፣ ወደ ውጪ በሚያሸሹ፣ በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በሚሳተፉ እና የ #ብሔራዊ_ባንክ የአሰራር እና የቁጥጥር ሥርዓት በሚጥሱ ላይ ጥብቅ የቁጥጥር እና የክትትል ስራም ይሰራል ብለዋል፡፡


በዚህ ሥራ የተሰማሩ ኩባንያዎች እና ፈቃድ የሌላቸው ኩባንያዎችና ግለሰቦች ከኢትዮጵያ የባንክ ስርዓት ጋር ያላቸው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ ይደረጋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡


ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የሰጣቸውን የሐዋላ ኩባንያዎች ስም ዝርዝር በባንኩ ድረ ገፁ እንደሚያሳውቅ የተናገሩት ገዥው ማሞ እስመለአለም ምህረቱ፤ ከዚያ ውጭ ያሉት በሙሉ ፈቃድ ያልተሰጣቸው እንደሆኑ መታወቅ አለበት፤ በዚህም ህብረተሰቡ ከስጋት፣ ከስርቆትና መጭበርበር ራሱን መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዛሬው እለት 50 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጨረታ አውጥቷል፡፡


የውጭ ምንዛሪ ጨረታ አካሄድ በማዕካላዊ ባንክ እየተከማቸ ካለው የውጭ ምንዛሪ የተወሰነውን መጠን ለግሉ ዘርፍ ለማቅረብና የማዕከላዊ ባንኩን የገንዘብ ፖሊሲ ዓላማ ለማሳካት የሚረዳ ይሆናል ተብሏል፡፡


ፍላጎቱ ያላቸው ባንኮች የጨረታ ሰነዶቻቸውን ዛሬ ከ4 ሰዓት አስከ 6 ሰዓት እንዲያስገቡ ባንኩ ጥሪ አቅርቧል፡፡


ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r


コメント


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page